መዝሙር 139:7-12
መዝሙር 139:7-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የድኅነቴ ኀይል፥ በጦርነት ቀን በራሴ ላይ ሁነህ ሰወርኸኝ። አቤቱ፥ ጌታዬ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኀጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፥ እንዳይታበዩም አትተወኝ። የአሽክላቸው ራስ የከንፈራቸውም ክፋት ይድፈናቸው። የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ መቆም እንዳይችሉ በችግር ወደ ምድር ይውደቁ። ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፤ ዐመፀኛ ሰውን ክፋት ለጥፋት ታድነዋለች። እግዚአብሔር ለድሆች ዳኝነትን ለችግረኞችም ፍርድን እንዲያደርግ ዐወቅሁ።
መዝሙር 139:7-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች። እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣ ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና።
መዝሙር 139:7-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ። ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም።
መዝሙር 139:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።