መዝሙር 139:1-24
መዝሙር 139:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ። አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች። እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣ ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና። አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ። አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው! ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው! ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር። ተኛሁም ነቃሁም፣ ገና ከአንተው ጋራ ነኝ። አምላክ ሆይ፤ ክፉዎችን ብትገድላቸው ምናለበት! ደም የተጠማችሁ ሰዎች ሆይ፤ ከእኔ ራቁ! ስለ አንተ በክፉ ሐሳብ ይናገራሉና፤ ጠላቶችህም ስምህን በከንቱ ያነሣሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚጠሉህን አልጠላምን? በአንተ ላይ የሚነሡትንስ አልጸየፍምን? በፍጹም ጥላቻ ጠልቻቸዋለሁ፤ ባላጋራዎቼም ሆነዋል። እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።
መዝሙር 139:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! መርምረህ ዐውቀኸኛል። አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሣ ታውቃለህ፤ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ። የምጓዝበትንና የማርፍበትን ቦታ ታስተውላለህ፤ ተግባሬን ሁሉ ታውቃለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ። በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ። የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው። ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ። ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም። ሁለንተናዬን የፈጠርክ አንተ ነህ፤ በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ። በሚያስፈራና በሚያስገርም ሁኔታ ስለ ተፈጠርኩ አመሰግንሃለሁ፤ ሥራዎችህ ሁሉ አስደናቂዎች መሆናቸውን ጠንቅቄም ዐውቃለሁ። በድብቁ ቦታ በተሠራሁ ጊዜና በጥልቁ መሬት ውስጥ በአንድነት በተገጣጠምኩ ጊዜ ሰውነቴ ለአንተ ድብቅ አልነበረም። ከመወለዴ በፊት አየኸኝ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል። አምላክ ሆይ! ሐሳብህ እጅግ የከበረና የሰፋ ስለ ሆነ እኔ ልረዳው አልችልም። ሐሳብህ ቢቈጠር ከባሕር አሸዋ የበዛ ነው፤ ቈጥሬ ልጨርስ ብፈልግ ዘለዓለማዊ መሆን ይኖርብኛል። አምላክ ሆይ! ምነው ክፉዎችን ባጠፋህ! ምነው የደም ሰዎችንም ከእኔ ባራቅህ! እነርሱ በአንተ ላይ ክፉ ነገር ይናገራሉ፤ በጠላትነትም ስምህን በክፉ ያነሣሉ። እግዚአብሔር ሆይ! የሚጠሉህን እጅግ እጠላቸዋለሁ! በአንተ ላይ የሚያምፁትንም እጅግ እጸየፋቸዋለሁ! በብርቱ እጠላቸዋለሁ፤ እንደ ጠላቶቼም እቈጥራቸዋለሁ። አምላክ ሆይ! መርምረኝ፤ ልቡናዬንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ። በእኔ ውስጥ በደል እንዳለ ተመልከት፤ በዘለዓለማዊውም መንገድ ምራኝ።
መዝሙር 139:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፥ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ጉዞዬንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። ከኋላና ከፊት ጠበቅኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ እጅጉን ያስደንቃል፥ ከከፍታውም ብዛት ልደርስበት አልችልም። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ ሐሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸውም እንደምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፥ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። አቤቱ፥ አንተ ክፉዉን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ “ከእኔ ፈቀቅ በሉ”። በክፋት ይናገሩብሃልና፥ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል። አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? በአንተ ላይ የሚነሡትንም አልናቅሁምን? ጨርሶ ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ። አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፥ ፈትነኝ መንገዴንም እወቅ፥ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፥ የዘለዓለምንም መንገድ ምራኝ።