መዝሙር 139:1-16
መዝሙር 139:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ። አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች። እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣ ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና። አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤ በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣ ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ።
መዝሙር 139:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! መርምረህ ዐውቀኸኛል። አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሣ ታውቃለህ፤ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ። የምጓዝበትንና የማርፍበትን ቦታ ታስተውላለህ፤ ተግባሬን ሁሉ ታውቃለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ። በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ። የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው። ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ። ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም። ሁለንተናዬን የፈጠርክ አንተ ነህ፤ በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ። በሚያስፈራና በሚያስገርም ሁኔታ ስለ ተፈጠርኩ አመሰግንሃለሁ፤ ሥራዎችህ ሁሉ አስደናቂዎች መሆናቸውን ጠንቅቄም ዐውቃለሁ። በድብቁ ቦታ በተሠራሁ ጊዜና በጥልቁ መሬት ውስጥ በአንድነት በተገጣጠምኩ ጊዜ ሰውነቴ ለአንተ ድብቅ አልነበረም። ከመወለዴ በፊት አየኸኝ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል።
መዝሙር 139:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፥ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ጉዞዬንና መኝታዬን አንተ መረመርህ፥ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። ከኋላና ከፊት ጠበቅኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ እጅጉን ያስደንቃል፥ ከከፍታውም ብዛት ልደርስበት አልችልም። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ቢሆን፥ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፥ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። አቤቱ፥ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፥ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዐይኖችህ አዩ፥ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።