መዝሙር 132:1-18
መዝሙር 132:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ዳዊትን፣ የታገሠውንም መከራ ሁሉ ዐስብ። እርሱ ለእግዚአብሔር ማለ፤ ለያዕቆብም ኀያል አምላክ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “ወደ ቤቴ አልገባም፤ ዐልጋዬም ላይ አልወጣም፤ ለዐይኖቼ እንቅልፍን፣ ለሽፋሽፍቶቼም ሸለብታ አልሰጥም፤ ለእግዚአብሔር ስፍራን፣ ለያዕቆብም ኀያል አምላክ ማደሪያን እስካገኝ ድረስ።” እነሆ፤ በኤፍራታ ሰማነው፤ በቂርያትይዓሪም አገኘነው። “ወደ ማደሪያው እንግባ፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንስገድ። እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፣ ከኀይልህ ታቦት ጋራ ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ። ካህናትህ ጽድቅን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም እልል ይበሉ።” ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት ስትል፣ የቀባኸውን ሰው አትተወው። እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፤ በማይታጠፍም ቃሉ እንዲህ አለ፤ “ከሆድህ ፍሬዎች አንዱን፣ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ። ወንዶች ልጆችህ ኪዳኔን፣ የማስተምራቸውንም ምስክርነቴን ቢጠብቁ፣ ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ፣ ለዘላለም ይቀመጣሉ።” እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፣ ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዷልና እንዲህ አለ፤ “ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ ፈልጌአታለሁና በርሷ እኖራለሁ። እጅግ አትረፍርፌ እባርካታለሁ፤ ድኾቿን እንጀራ አጠግባለሁ። ለካህናቷ ድነትን አለብሳለሁ፤ ቅዱሳኗም በደስታ ይዘምራሉ። “በዚህም ለዳዊት ቀንድ አበቅላለሁ፤ ለቀባሁትም ሰው መብራት አዘጋጃለሁ። ጠላቶቹን ኀፍረት አከናንባቸዋለሁ፤ እርሱ ግን በራሱ ላይ የደፋው ዘውድ ያበራል።”
መዝሙር 132:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ልቤ በኩራት የተወጠረ አይደለም፤ ዳዊትን አስታውሰው፤ የተቀበለውን መከራ ሁሉ አትርሳ። እግዚአብሔር ሆይ! ለአንተ የገባውን ቃል ኪዳንና ሁሉን ለምትችል ለያዕቆብ አምላክ ለአንተ እንዲህ ሲል የተሳለውን ስእለት አስታውስ፤ “ለእግዚአብሔር የመኖሪያ ስፍራ እስከማዘጋጅ፥ ለያዕቆብ አምላክ ቤት እስከምሠራ ድረስ፥ ወደ ቤት አልገባም፤ ወይም በአልጋ ላይ አልተኛም፤ ዕረፍት ወይም እንቅልፍ አይኖረኝም።” በኤፍራታ ሆነን ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሰማን፤ በጁአሪም ምድር አገኘነው። ከዚህ በኋላ “ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ፤ በእግሩ ማረፊያ ሥር እንስገድ” አልን። እግዚአብሔር ሆይ! የኀይልህ መግለጫ ከሆነችው ከቃል ኪዳን ታቦት ጋር ወደምታርፍበት ወደ ቤተ መቅደስ ግባ። ካህናትህ የጽድቅን ሥራ ይሥሩ! ታማኞችህ በደስታ ይዘምሩ! ስለ አገልጋይህ ስለ ዳዊት ስትል መርጠህ የቀባኸውን አትተወው። እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል የማይሻር ቃል ኪዳን ገባለት፦ “ከልጆችህ አንዱን አነግሠዋለሁ፤ ልጆችህ ቃል ኪዳኔንና የምሰጣቸውን ትእዛዞች ከጠበቁ ልጆቻቸው ከአንተ በኋላ ለዘለዓለም ይነግሣሉ።” እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታል፤ መኖሪያውም ሊያደርጋት ይፈልጋል። ይህች የዘለዓለም ማረፊያ ስፍራዬ ናት፤ በዚያች ለመኖር እመኝ ስለ ነበር መኖሪያዬ አደረግኋት። ለጽዮን ምግብዋን አበዛለሁ፤ ድኾችዋንም እስከሚጠግቡ አበላቸዋለሁ። ካህናትዋን በሚያደርጉት ሁሉ እባርካቸዋለሁ፤ በውስጥዋም የሚኖሩ ታማኞች በደስታ ይዘምራሉ። ከዳዊት ዘር ንጉሥ እንዲወጣ አደርጋለሁ፤ የቀባሁትንም ኀያል አደርገዋለሁ። ጠላቶቹ ኀፍረትን እንዲከናነቡ አደርጋቸዋለሁ፤ እርሱ ግን የሚያንጸባርቅ ዘውድ ይቀዳጃል።
መዝሙር 132:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ዳዊትን፥ መከራውንም ሁሉ አስታውስ፥ ለጌታ እንደማለ፥ ለያዕቆብም ኀያል እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዐይኖቼም መኝታ፥ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ አልሰጥም፥ ለጌታ ስፍራ፥ ለያዕቆብ ኀያል ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በጁኦሪም ምድር አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንግባ፥ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንስገድ። አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት። ካህናትህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ጻድቃንህም ደስ ይበላቸው። ስለ ዳዊት ስለ ባርያህ ብለኽ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ። ጌታ ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ፦ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ። ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተማራቸውን ኪዳኔን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ። ጌታ ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ “ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፥ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። ስንቆቿን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ። ካህናትዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ጻድቃኗም እጅግ ደስ ይላቸዋል። በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ። ጠላቶቹንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፥ በእርሱ ግን ዘውዱ ያንጸባርቃል።”