መዝሙር 122:1-9
መዝሙር 122:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ” ባሉኝ ጊዜ፣ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እግሮቻችን ከደጅሽ ውስጥ ቆመዋል። ኢየሩሳሌም እጅግ እንደ ተጠጋጋች፣ ከተማ ሆና ተሠርታለች። ለእስራኤል በተሰጠው ሥርዐት መሠረት፣ የእግዚአብሔርን ስም ለማመስገን፣ የእግዚአብሔር ነገዶች ወደዚያ ይመጣሉ። በዚያም የፍርድ ዙፋኖች የሆኑት፣ የዳዊት ቤት ዙፋኖች ተዘርግተዋል። እንዲህ ብላችሁ ለኢየሩሳሌም ሰላም ጸልዩ፤ “የሚወድዱሽ ይለምልሙ፤ በቅጥርሽ ውስጥ ሰላም ይሁን፤ በምሽግሽም ውስጥ መረጋጋት ይስፈን”። ስለ ወንድሞቼና ስለ ባልንጀሮቼ፣ “በውስጥሽ ሰላም ይስፈን” እላለሁ። ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት፣ በጎነትሽን እሻለሁ።
መዝሙር 122:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ!” ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ! በበሮችሽ ገብተን በውስጥ ቆመናል። ኢየሩሳሌም እርስ በርስዋ ተጠጋግታና ተጠናክራ የተሠራች ከተማ ናት። በትእዛዙ መሠረት ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ የሚሰበሰቡት ወደዚህች ከተማ ነው። ከዳዊት ዘር የነገሡ ሁሉ ሕዝባቸውን ለመዳኘት በዚህች ከተማ ይቀመጡ ነበር። በኢየሩሳሌም ከተማ ሰላም እንዲሆን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “የሚወዱሽ ሁሉ ይበልጽጉ፤ በቅጥሮችሽ ውስጥ ሰላም ይሁን፤ በቤተ መንግሥትሽም ውስጥ ጸጥታ ይኑር።” በዘመዶቼና በወዳጆቼ ምክንያት ኢየሩሳሌምን “ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን!” እላታለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ! በአምላካችን በእግዚአብሔር ቤት ምክንያት ለአንቺ መልካም ነገር እንዲሆንልሽ እመኛለሁ።
መዝሙር 122:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ጌታ ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ። ኢየሩሳሌምስ እርስ በርስዋ እንደ ተገጠገጠች ከተማ ተሠርታለች። የጌታን ስም ያመሰግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የጌታ ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ። ዙፋኖች በዚያ ለፍርድ ተቀምጠዋልና፥ የዳዊት ቤት ዙፋኖች። ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ፥ አንተንም ለሚወድዱ መረጋጋት ይሁን። በቅጥሮችሽ ውስጥ ሰላም፥ በግምቦችሽም ውስጥ መረጋጋት ይሁን። ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም፦ “በውስጥሽ ሰላም ይሁን” ልበል። ስለ ጌታ አምላካችን ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ።