መዝሙር 119:97-105
መዝሙር 119:97-105 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ትእዛዞችህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ። አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም። ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።
መዝሙር 119:97-105 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ። ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል። ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ። ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥ ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ። ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥ መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ። ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው! ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል። ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ። ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው።
መዝሙር 119:97-105 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፥ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፥ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።