መዝሙር 119:56-62 - Compare All Versions
መዝሙር 119:56-62 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች። እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ። በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ። መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።
መዝሙር 119:56-62 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ።
መዝሙር 119:56-62 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ። ጌታ ድርሻዬ ነው፥ ቃልህን እጠብቃለሁ አልሁ። በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፥ እንደ ቃልህ ማረኝ። ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፥ ሕግህን ግን አልረሳሁም። ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ።