መዝሙር 119:1-8
መዝሙር 119:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብፁዓን ናቸው፤ መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ፤ ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔር ሕግ፤ ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት፤ ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ። ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል። ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ! ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም። የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣ በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ። ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ ፈጽመህ አትተወኝ።
መዝሙር 119:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው። ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥ የተባረኩ ናቸው። የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤ በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤ ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን በብርቱ እመኛለሁ። ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም። የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ።
መዝሙር 119:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመንገዳቸው እንከን የሌለባቸው፥ በጌታም ሕግ የሚመላለሱ ምስጉኖች ናቸው። ሕጉን የሚጠብቁ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፥ ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። ሕጎችህን በሚገባ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ደንቦችህን ለመጠበቅ መንገዶቼ ምነው በቀኑ። ትእዛዞችህንም ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርምና። አቤቱ፥ ትክክለኛ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፥ በፍጹም አትጣለኝ።