መዝሙር 118:1-9
መዝሙር 118:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመንገዳቸው ንጹሓን የሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ብፁዓን ናቸው። ምስክሩን የሚፈልጉ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ብፁዓን ናቸው፤ ዐመፃን የሚያደርጉ ግን በመንገዱ አይሄዱም። ትእዛዛትህን እጅግ ይጠብቁ ዘንድ አንተ አዘዝህ። ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ የሚቀናስ ከሆነ መንገዴ ይቅና። ትእዛዝህን ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርም። አቤቱ፥ የጽድቅህን ፍርድ ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ፤ ለዘለዓለም አትጣለኝ። ጐልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።
መዝሙር 118:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል። የአሮን ቤት፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበሉ። በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ። ሰውን መከታ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
መዝሙር 118:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ። የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት የአሮን ልጆች ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። የሚፈሩት ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። በተጨነቅሁ ጊዜ ጩኸቴን ወደ እግዚአብሔር አሰማሁ፤ እርሱም ሰማኝ፤ ነጻም አወጣኝ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ አልፈራም፤ ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ፥ የጠላቶቼን ውድቀት አያለሁ። በሰው ከመመካት ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በመሪዎች ከመመካት ይልቅ፥ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
መዝሙር 118:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ ጌታን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ። በተጨነቅሁ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ መለሰልኝ፥ አሰፋልኝም። ጌታ ከጎኔ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? ጌታ ሊረዳኝ ከጎኔ ነው፥ እኔም ጠላቶቼን በኩራት አያለሁ። በሰው ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል። በኃያላን ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል።