መዝሙር 112:1-10

መዝሙር 112:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ይመስገን! እግዚአብሔርን የሚፈራና ትእዛዞቹንም በመፈጸም እጅግ ደስ የሚለው ሰው እንዴት የተባረከ ነው! የደግ ሰው ልጆች በምድር ላይ ብርቱዎች ይሆናሉ፤ የቅኖች ትውልድ ይባረካል። ቤተሰቦቹ ሀብታሞችና ባለጸጎች ይሆናሉ፤ ጽድቅም ለዘለዓለም የእርሱ ይሆናል። ምሕረትና ቸርነት፥ ቅንነትም ለሚያደርግ ለደግ ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል። ሥራውን በቅንነት የሚመራ፥ ለጋሥ የሆነና ሳይሰስት የሚያበድር ኑሮው የተሳካለት ይሆናል። በእውነት እርሱ ምንጊዜም ቢሆን አይናወጥም፤ ጻድቅ ሰው ለዘለዓለም ይታሰባል። እምነቱ ጽኑ ስለ ሆነና በእግዚአብሔርም ስለሚተማመን፥ ክፉ ወሬ አያስደነግጠውም። በእግዚአብሔር ያለው እምነት እጅግ የጸና ስለ ሆነ ከቶ አይፈራም፤ በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል። ለችግረኞች በልግሥና ይሰጣል፤ ቸርነቱም የማያቋርጥ ነው፤ ኀይልንና ክብርን ይጐናጸፋል። ክፉዎች ይህን አይተው ይቈጣሉ፤ ተስፋ በመቊረጥም ጥርሳቸውን ያፋጫሉ፤ የክፉዎችም ምኞት ከንቱ ይሆናል።