መዝሙር 111:2-10
መዝሙር 111:2-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤ የጻድቃን ትውልዶች ይባረካሉ። ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል። ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፤ አምላካችንም ጻድቅ ነው። ርኅሩኅ፥ ይቅር ባይና ቸር ሰው ነገሩን በፍርድ ይፈጽማል። ለዘለዓለም አይታወክም፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል። ከክፉ ነገርም አይፈራም፤ በእግዚአብሔር ለመታመን ልቡ የጸና ነው። በጠላቶቹ ላይ እስኪያይ ድረስ ልቡ ጽኑዕ ነው፥ ለዘለዓለምም አይታወክም። በተነ፥ ለችግረኞችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘለዓለም ዓለም ይኖራል፤ ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል። ኀጢአተኛም አይቶ ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፤ የኃጥኣንም ምኞት ትጠፋለች።
መዝሙር 111:2-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፤ ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል። ሥራው ባለክብርና ባለግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ርኅሩኅም ነው። ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል። ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣ የአሠራሩን ብርታት አሳይቷል። የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤ ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤ ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤ በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው። ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።
መዝሙር 111:2-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አድርጎአል፤ በእርሱ አስደናቂ ሥራዎች የሚደሰት ሁሉ ያስባቸዋል። የእግዚአብሔር ሥራ በክብርና በግርማ የተሞላ ነው፤ ጽድቁም ዘለዓለማዊ ነው። እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ በአስደናቂ ሥራውም የገነነ ነው። ለሚፈሩት ሁሉ ምግባቸውን ያዘጋጅላቸዋል፤ ቃል ኪዳኑንም ከቶ አይረሳም። የሕዝቦችን ርስት በመስጠት ታላቅ ኀይሉን ለወገኖቹ አሳይቶአል። የሚያደርገው ሁሉ እውነትና ትክክል ነው፤ ትእዛዞቹም የታመኑ ናቸው። እነርሱም ለዘለዓለም የጸኑ ናቸው፤ የተሰጡትም በእውነትና በታማኝነት ነው። ለድኾች በልግሥና ይሰጣል፤ ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳኑንም ሰጠ፤ ስሙም ቅዱስና አስፈሪ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙን የሚፈጽሙትን ሁሉ አስተዋዮች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን!
መዝሙር 111:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታ ሥራዎች ታላላቅ ናቸው፥ ደስ በሚሰኙባቸው ሁሉ ይፈለጋሉ። ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፥ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል። ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፥ ጌታ መሓሪና ርኅሩኅ ነው። ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፥ ኪዳኑንም ለዘለዓለም ያስባል። የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ። የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ናቸው፥ ትእዛዛቱም በሙሉ የታመኑ ናቸው፥ ለሁልጊዜና ዘለዓለምም የጸኑ ናቸው፥ በእውነትና በጽድቅም የተሠሩ ናቸው። ለሕዝቡ መዳንን ላከ፥ ኪዳኑንም ለዘለዓለም ደነገገ፥ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው። የጥበብ መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ የሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋልን ያገኛሉ፥ ውዳሴውም ለዘለዓለም ይኖራል።