መዝሙር 11:1-7
መዝሙር 11:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ አድነኝ፥ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና። እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ። የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውንም ምላስ፤ “ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈሮቻችን የእኛ ናቸው፥ ጌታችን ማን ነው?” የሚሉትን። “ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ እስረኞችም ጩኸት እግዚአብሔር ይላል፥ አሁን እነሣለሁ፤ መድኀኒትን አደርጋለሁ፥ በእርሱም እገልጣለሁ።” በምድር ላይ እንደ ተፈተነ፥ ሰባት ጊዜም እንደ ተጣራ ብር የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው። አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘለዓለም ታደገን።
መዝሙር 11:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ ታዲያ ነፍሴን፣ “እንደ ወፍ ወደ ተራራ ብረሪ” ለምን ትሏታላችሁ? ደግሞም ለምን እንዲህ ትሉኛላችሁ? “ክፉዎች፣ እነሆ፤ ቀስታቸውን ገትረዋል፤ የቅኑን ሰው ልብ በጨለማ ለመንደፍ፣ ፍላጻቸውን በአውታሩ ላይ ደግነዋል። መሠረቱ ከተናደ፣ ጻድቅ ምን ማድረግ ይችላል?” እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን በሰማይ ነው። ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። እግዚአብሔር ጻድቁንና ክፉውን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወድዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች። እርሱ በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምና ዲን ያዘንባል፤ የጽዋቸውም ዕጣ ፈንታ፣ የሚለበልብ ዐውሎ ነፋስ ነው። እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፤ የጽድቅ ሥራም ይወድዳል፤ ቅኖችም ፊቱን ያያሉ።
መዝሙር 11:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ከለላዬ ነው፤ እንዴት “እንደ ወፍ ወደ ተራራዎች ሽሽ” ትሉኛላችሁ። ኃጢአተኞች በጨለማ አድብተው ልበቅኖችን ለመግደል ቀስታቸውን ገትረዋል፤ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋል። መሠረቶች ሲፈርሱ ጻድቅ ሰው ምን ማድረግ ይችላል? እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ ነው፤ ዙፋኑም በሰማይ ነው፤ የሰውን ልጆች ይመለከታል። አተኲሮም በማየት ዐይኖቹም ይመረምሩአቸዋል። እግዚአብሔር ጻድቃንንና ኃጢአተኞችን ይፈትናል፤ ዐመፅ የሚወዱትን ግን ይጠላቸዋል። በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምንና ዲንን ያዘንባል፤ የሚጋረፍ ነፋስም የእነርሱ ዕድል ፈንታ ነው። እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ የጽድቅን ሥራ ይወዳል፤ ትክክለኛ ሥራ የሚሠራ ሰው ሁሉ ፊቱን ያያል።
መዝሙር 11:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጌታ ታመንሁ፥ ነፍሴን፦ እንዴት እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ሽሺ ትሉአታላችሁ? እነሆ ክፉዎች ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ። መሠረቶቹ ከፈረሱ፥ ጻድቅ ምን ማድረግ ይችላል? ጌታ በተቀደሰው መቅደሱ ነው፥ ጌታ፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፥ ዐይኖቹ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። ጌታ ጻድቅንና ክፉን ይመረምራል፥ ዓመፃ የሚወደውን ግን ነፍሱ ትጠላለች። በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምንና ዲንን ያዘንባል የሚያቃጥል ነፋስም የጽዋቸው እድል ፈንታ ነው። ጌታ ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፥ ቅን ሰው ፊቱን ያየዋል።