መዝሙር 107:13-21
መዝሙር 107:13-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤ እስራታቸውንም በጠሰላቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የናሱን በሮች ሰብሯልና፤ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧል። አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ። ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
መዝሙር 107:13-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤ የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። ከናስ የተሠሩትን በሮች ሰባበረ፤ የብረት መወርወሪያዎችንም ቈራረጠ። የዐመፅን መንገድ በመከተላቸው አንዳዶቹ ሞኞች ነበሩ ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ተቀጥተውበታል። ምግብ ስላስጠላቸው፥ ለመሞት ተቃርበው ነበር። ከዚህ በኋላ በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እነርሱን ለመፈወስ ቃሉን ላከ፤ ከሞትም አዳናቸው። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
መዝሙር 107:13-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ ሰንሰለታቸውንም በጣጠሰ። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የናሱን ደጆች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈራርጦአልና። በዓመፅ መንገዳቸው አላዋቂ ሆኑ፥ በጥፋታቸው ተጎሳቆሉ። ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜም ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከአዘቅትም አዳናቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥