መዝሙር 107:1-43
መዝሙር 107:1-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና። እግዚአብሔር የተቤዣቸው፣ ከጠላት እጅ የታደጋቸው ይህን ይበሉ፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ። አንዳንዶቹ ጭው ባለ በረሓ ተቅበዘበዙ፤ ወደሚኖሩባት ከተማ የሚያደርስ መንገድ ዐጡ። ተራቡ፤ ተጠሙ፤ ነፍሳቸውም በውስጣቸው ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ወደሚኖሩባትም ከተማ፣ በቀና መንገድ መራቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤ የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል። አንዳንዶቹ በብረት ሰንሰለት ታስረው የተጨነቁ፣ በጨለማ፣ በጥልማሞት ውስጥ የተቀመጡ ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማመፅ፣ የልዑልን ምክር አቃልለዋልና። ስለዚህ በጕልበት ሥራ ልባቸውን አዛለ፤ ተዝለፈለፉ፤ የሚደግፋቸውም አልነበረም። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤ እስራታቸውንም በጠሰላቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ እርሱ የናሱን በሮች ሰብሯልና፤ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧል። አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ። ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ። አንዳንዶቹ በመርከብ ወደ ባሕር ወረዱ፤ በታላቅም ውሃ ላይ ሥራቸውን አከናወኑ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በዚያ አዩ፤ ድንቅ አድራጎቱንም በጥልቁ ውስጥ ተመለከቱ። እርሱ ተናግሮ ዐውሎ ነፋስን አስነሣ፤ ነፋሱም ማዕበሉን ከፍ ከፍ አደረገ። ወደ ሰማይ ወጡ፤ ወደ ጥልቅም ወረዱ፤ ከመከራቸውም የተነሣ ሐሞታቸው ፈሰሰ። እንደ ሰከረ ሰው ዞሮባቸው ወዲያ ወዲህ ተንገዳገዱ፤ መላው ጠፍቶባቸው የሚያደርጉትን ዐጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ፤ የባሕሩም ሞገድ ረጭ አለ። ጸጥ በማለቱም ደስ አላቸው፤ ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፤ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ይወድሱት። ወንዞችን ወደ ምድረ በዳ፣ የውሃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ ምድር ለወጠ። ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣ ፍሬያማዋን ምድር በጨው የተበከለች አደረጋት። ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣ ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ። የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤ ብዙ ፍሬም አመረቱ። ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም። በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤ በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤ መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው። ድኾችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤ ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ። ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤ ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች። እንግዲህ ማንም ብልኅ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።
መዝሙር 107:1-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ! እግዚአብሔር የተቤዣቸው ከችግርም ያዳናቸው ሁሉ እንዲሁ ይበሉ። ከባዕድም አገር መልሶ አምጥቶአችኋል፤ ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ሰብስቦአችኋል። አንዳንዶች የመንገዳቸውን አቅጣጫ በመሳት በበረሓ ተንከራተቱ፤ ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ የሚመራቸውን መንገድ ለማግኘት አልቻሉም። ተርበውና ተጠምተው ስለ ነበር፥ ተስፋ ቈረጡ። በመከራቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እግዚአብሔርም ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ በትክክለኛ መንገድ መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ እግዚአብሔርን ያመስግኑ። እርሱ የተጠሙትን ያረካቸዋል፤ የተራቡትንም ብዙ መልካም ነገር በመስጠት ያጠግባቸዋል። ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ በሰንሰለትም ታስረው ይኖሩ ነበር። ይህም ሁሉ የደረሰባቸው በልዑል እግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፃቸውና ምክሩንም በመናቃቸው ነበር። በከባድ ሥራ እንዲጨነቁ አደረጋቸው፤ የሚረዳቸውም ባለማግኘታቸው ተሰናክለው ወደቁ። በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤ የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። ከናስ የተሠሩትን በሮች ሰባበረ፤ የብረት መወርወሪያዎችንም ቈራረጠ። የዐመፅን መንገድ በመከተላቸው አንዳዶቹ ሞኞች ነበሩ ሕግን በመተላለፋቸው ምክንያት ተቀጥተውበታል። ምግብ ስላስጠላቸው፥ ለመሞት ተቃርበው ነበር። ከዚህ በኋላ በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። እነርሱን ለመፈወስ ቃሉን ላከ፤ ከሞትም አዳናቸው። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ በደስታ መዝሙርም ሥራውን ይግለጡ። አንዳንዶች በመርከብ ተሳፍረው በታላቅ በባሕር ላይ እየተጓዙ ንግዳቸውን ያካሂዱ ነበር። እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አዩ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ተመለከቱ። ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ዐውሎ ነፋስ ነፈሰ፤ ማዕበሉም ተንቀሳቀሰ። መርከበኞቹ በሞገዱ ኀይል ተገፍትረው ወደ ላይ ወጡ፤ ተመልሰውም ወደ ጥልቁ ወረዱ፤ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ተዋከቡ። እንደ ሰካራም ዞረባቸው፤ ተንገዳገዱም፤ የማስተዋል ችሎታቸው ሁሉ ጠፋ። በመከራቸው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱንና ማዕበሉን ጸጥ አደረገ። በጸጥታውም ምክንያት ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ በሰላም አደረሳቸው። ስላደረገላቸው ድንቅ ነገሮችና ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመስግኑ። በሕዝብ ጉባኤ መካከል ታላቅነቱንም ያብሥሩ፤ በሽማግሌዎች ሸንጎ ያመስግኑት። እግዚአብሔር ወንዞች ፈጽመው እንዲደርቁ፥ ምንጮችም እንዳይፈስሱ አደረገ። እዚያ ከሚኖሩት ሰዎች ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን አገር እንደ ጨው ምድር የማታፈራ አደረጋት። እንደገናም በበረሓው ብዙ ኲሬዎች እንዲኖሩ፥ በደረቁም ምድር ብዙ ምንጮች እንዲገኙ አደረገ። የተራቡ ሕዝቦች በዚያ እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሠሩ። በእርሻዎች ላይ እህልን ዘሩ፤ ወይንን ተከሉ፤ ብዙ መከርም ሰበሰቡ። ሕዝቡን ባረካቸው፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ፤ የከብቶቻቸውም ቊጥር እንዳያንስ አደረገ። በጭቈና፥ በችግርና በሐዘን ተሸንፈው በተዋረዱ ጊዜ ግን፥ እግዚአብሔር ልዑላኑን አዋረደ፤ በምድረ በዳም አሸዋ ውስጥ እንዲንከራተቱ አደረገ። ችግረኞችንም ከሥቃያቸው አወጣቸው፤ እንደ በግ መንጋ የበዙ ልጆችንም ሰጣቸው። ቅኖች ይህን በማየት ደስ ይላቸዋል፤ ክፉዎች ግን ዐፍረው ዝም ይላሉ። ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ ይህን ያስተውሉ፤ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ ይገንዘቡ።
መዝሙር 107:1-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሃሌ ሉያ! ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ፥ ጌታ የታደጋቸው፥ ከጠላትም እጅ ያዳናቸው ይናገሩ። ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው። በበረሃ፥ በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፥ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። ተራቡ፥ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም ዛለች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፥ ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ በቀና መንገድን መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የተጠማችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራበችን ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና። በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ ልባቸው በድካም ተዋረደ፥ ተሰናከሉ የሚረዳቸውም አጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ ሰንሰለታቸውንም በጣጠሰ። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የናሱን ደጆች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈራርጦአልና። በዓመፅ መንገዳቸው አላዋቂ ሆኑ፥ በጥፋታቸው ተጎሳቆሉ። ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። በተጨነቁ ጊዜም ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከጭንቀታቸው አዳናቸው። ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከአዘቅትም አዳናቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ጽኑ ፍቅሩም ጌታን ያመስግኑ፥ የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ። በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላላቅ ውኆች ሥራቸውን የሚሠሩ፥ እነርሱ የጌታን ሥራ፥ በታላቅ አዘቅትም ያሉትን ድንቅ ሥራዎች አዩ። ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገዶችንም አስነሣ። ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፥ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች። ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱን አስቆመ፥ ሞገዱም ጸጥ አለ። ዝም ብለዋልና ደስ አላቸው፥ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው። ስለ ጽኑ ፍቅሩ፥ ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ጌታን ያመስግኑ። በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት። ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ መሬት አደረገው፥ ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት። ምድረ በዳን ወደ ውኃ ማጠራቀምያ፥ ደረቁንም ምድር ወደ ውኃ ምንጭነት ቀየረ። በዚያም ረሀብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። እርሻዎችንም ዘሩ፥ ወይኖችንም ተከሉ፥ ፍሬንም ሰበሰቡ። ባረካቸውም እጅግም በዙ፥ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም። እነርሱ በጭቈና፥ በስቃይና በኃዘን ተዋርደው እያነሱ ሄዱ፥ በመኰንኖችም ላይ ውርደትን ዘረገፈ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አንከራተታቸው። ችግረኛንም ከመከራው አወጣው፥ ቤተሰቦችን እንደ በጎች መንጋ አበዛ። ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፥ ክፋት በሙሉ አፉን ይዘጋል። ጠቢብ ማነው? ይህንን ይፈጽም፥ እርሱ የጌታንም ጽኑ ፍቅር ይገነዘባል።