መዝሙር 105:1-45
መዝሙር 105:1-45 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። የእግዚአብሔርን ኀይል ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ይሰማ ዘንድ ማን ያደርጋል? ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው። አቤቱ፥ ሕዝብህን በይቅርታህ ዐስበን፥ በማዳንህም ይቅር በለን፤ የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንከብር ዘንድ። ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአት ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም። አባቶቻችን በግብፅ ሀገር ሳሉ ተአምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ አስመረሩህ። ኀይሉን ያሳያቸው ዘንድ ስለ ስሙ አዳናቸው። የኤርትራንም ባሕር ገሠጻት፥ ደረቀችም፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው። ከጠላቶቻቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላቶቻቸውም እጅ ተቤዣቸው። ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። ያንጊዜም በቃሉ አመኑ፥ በምስጋናውም አመሰገኑት። ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልጸኑም። በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን አሳዘኑት። የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳችውም ጥጋብን ላከ። ሙሴንም፥ እግዚአብሔር የቀደሰውን አሮንንም በሰፈር አስቈጧቸው። ምድር ተከፈተች፥ ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤ በማኅበራቸው እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኃጥኣንን አቃጠላቸው። በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ሣርንም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ። ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ። ታላቅ ነገርንም በግብፅ፥ ድንቅንም በካም ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን። እንዳያጠፋቸው የቍጣውን መቅሠፍት ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ባጠፋቸው ነበር አለ። የተወደደችውንም ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥ በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰሙም። እጁንም አነሣባቸው። በምድረ በዳ ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየሀገሩም ይበትናቸው ዘንድ። በብዔል ፌጎርም ዐለቁ፥ የሞተ መሥዋዕትንም በሉ፤ በሥራቸውም አነሣሱት ቸነፈርም በላያቸው በዛ። ፊንሐስም ተነሥቶ አዳናቸው፥ ቸነፈሩም ተወ። ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ በከንፈሮቹም አዘዘ። እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ በደልም ሆነባቸው። ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፤ ንጹሕ ደምንም አፈሰሱ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች ሠዉ፥ ምድርም በደም ታለለች። በሥራቸውም ረከሰች፥ በጣዖታቸውም አመነዘሩ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ቍጣን ተቈጣ፥ ርስቱንም ተጸየፈ። በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው። ጠላቶቻቸውም አሠቃዩአቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ። ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ እነርሱ ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኀጢአታቸውም መከራ ተቀበሉ። እንደ ተጨነቁም ተመለከታቸው፥ ጸሎታቸውንም ሰማቸው፤ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት አዘነላቸው።
መዝሙር 105:1-45 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም በሕዝቦች መካከል አሳውቁ። ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤ ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ። እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ። ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤ እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣ ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ። እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው። ኪዳኑን ለዘላለም፣ ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል። ከአብርሃም ጋራ የገባውን ቃል ኪዳን፣ ለይሥሐቅም የማለውን መሐላ አይረሳም። ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣ ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤ እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣ የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።” ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣ በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣ ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣ ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው ተንከራተቱ፣ ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።” በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤ የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤ በባርነት የተሸጠውን ሰው፣ ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ። እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ። የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤ የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው። የቤቱ ጌታ፣ የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤ ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣ ሽማግሌዎቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር። እስራኤል ወደ ግብጽ ገባ፤ ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ። እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤ ሕዝቡን እንዲጠሉ፣ በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ። ባሪያውን ሙሴን፣ የመረጠውንም አሮንን ላከ። እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣ ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ። ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤ እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ። ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ዓሦቻቸውንም ፈጀ። ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣ ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው። እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤ ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤ ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤ የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ። እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤ ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤ የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤ የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤ ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣ የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ። የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤ ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም። እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣ ወጥተው ሲሄዱ ግብጽ ደስ አላት። ደመናን እንደ መጋረጃ ዘረጋላቸው፤ እሳትም በሌሊት አበራላቸው። በለመኑትም ጊዜ፣ ድርጭት አመጣላቸው፤ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለደለ፤ እንደ ወንዝም በበረሓ ፈሰሰ። ለባሪያው ለአብርሃም የሰጠውን፣ ቅዱስ የተስፋ ቃሉን አስቧልና። ሕዝቡን በደስታ፣ ምርጦቹንም በእልልታ አወጣቸው። የሌሎችን ሕዝቦች ምድር ሰጣቸው፤ የእነዚህንም የድካም ፍሬ ወረሱ፤ ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ፣ ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው።
መዝሙር 105:1-45 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ ያደረገውንም ሁሉ ለአሕዛብ ንገሩ። ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤ ያደረገውንም አስደናቂ ነገር ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ደስ ይበላችሁ! እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሐሴት ያድርግ! በእግዚአብሔርና በኀያል ሥልጣኑ ተማመኑ፤ ዘወትርም እርሱን ፈልጉ። አገልጋዮች የሆናችሁ የእስራኤል ልጆች ሆይ! የእግዚአብሔር ምርጥ የሆናችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች፥ የሰጠውን ፍርድና ያደረጋቸውን ተአምራት አስታውሱ። እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በዓለም ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ወይም የሰጠውን ተስፋ እስከ ሺህ ትውልድም ሆነ ለዘለዓለም አይረሳም። ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠብቃል፤ ለይስሐቅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸናል። ለያዕቆብ ሥርዓት፥ ለእስራኤልም ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አድርጎ አጸናው። ይህም ቃል ኪዳን “የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፤ ለአንተም የተመደበ ርስት ይሆናል” የሚል ነው። ይህም የሆነው እነርሱ በቊጥር አነስተኞች ለሀገሩም እንግዶች ሆነው ሳለ ነው። ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ፥ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተንከራተቱ። እግዚአብሔር ግን ማንም እንዲጨቊናቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። “የተመረጡ አገልጋዮቼን አትንኩ፤ ነቢያቴንም አትጒዱ” በማለት አስጠነቀቃቸው። እግዚአብሔር ራብን በአገራቸው ላይ አመጣ፤ ምግባቸውንም ሁሉ አጠፋ። ነገር ግን ከእነርሱ አንዱን ሰው አስቀድሞ ላከ፤ እርሱም እንደ ባሪያ የተሸጠው ዮሴፍ ነበር። እግሮቹ በእግር ብረት ታስረው ነበር፤ በአንገቱም የብረት ቀለበት ነበር። ዮሴፍ ራሱ አስቀድሞ የተናገረው እስኪፈጸም ድረስና የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነቱን እስኪያረጋግጥለት ድረስ ነው። ከዚያ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ዮሴፍን ነጻ አደረገው። በመንግሥቱ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው፤ በምድሩም ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፤ በንጉሡ ባለሥልጣኖች ላይ አዛዥ ሆነ፤ ለንጉሡም አማካሪዎች ጥበብን ያስተምራቸው ዘንድ ሥልጣን ተሰጠው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ፤ በዚያም አገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ። እግዚአብሔር ወገኖቹን አበዛቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። እግዚአብሔር ግን ወገኖቹን እንዲጠሉና፥ በአገልጋዮቹም ላይ በተንኰል እንዲነሡ ግብጻውያንን አስጨከነ። ከዚህ በኋላ አገልጋዩን ሙሴንና የመረጠውን አሮንን ላከ። እነርሱ በግብጽ ምድር የእግዚአብሔርን ድንቅ ነገሮችና ተአምራትን አደረጉ። እግዚአብሔር በአገሩ ላይ ጨለማ እንዲሆን አደረገ፤ ይሁን እንጂ ግብጻውያን ትእዛዞቹን አልፈጸሙም። የወንዞቻቸውንም ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤ ዓሣዎቻቸውንም ሁሉ ገደለ። አገራቸው በእንቁራሪት ተሸፈነች፤ ቤተ መንግሥቱ እንኳ ሳይቀር ሁሉ ቦታ በእንቁራሪት ተሞላ። ተናካሽ ዝንቦችና ተናካሽ ትንኞች በአገሩ ሁሉ ላይ እንዲርመሰመሱ አዘዘ። እግዚአብሔር በአገራቸው ላይ በዝናብ ፈንታ የበረዶ ናዳንና መብረቅን አወረደ። የወይን ተክሎቻቸውንና የበለስ ዛፎቻቸውን አጠፋ፤ ሌሎቹንም ዛፎቻቸውን ሁሉ ሰባበረ። እርሱ ባዘዘው መሠረት ሊቈጠር የማይችል የአንበጣና የኲብኲባ መንጋ መጣ። በምድሩ ላይ ያለውን ለምለም ተክልና ሰብል ሁሉ በልተው እንዲጨርሱ አደረገ፤ የእያንዳንዱን ግብጻዊ ቤተሰብ የበኲር ልጅ ገደለ። ከዚህ በኋላ እስራኤላውያንን መርቶ አወጣ፤ ሲወጡም ብርና ወርቅ ይዘው ነበር፤ ከነገዶቻቸውም መካከል ወደ ኋላ የቀረ ማንም አልነበረም። ግብጻውያንም እጅግ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፤ በመውጣታቸው ተደሰቱ። በሚሄዱበትም ጊዜ በደመና ጋረዳቸው፤ በሌሊትም፥ ብርሃን የሚሰጣቸውን እሳት አዘጋጀላቸው። ምግብ በጠየቁት ጊዜ ድርጭቶችን ላከላቸው። ከሰማይ እንጀራን ልኮ አጠገባቸው። አለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ወጣ፤ በበረሓውም ውስጥ እንደ ወንዝ ውሃ ፈሰሰ። ለአገልጋዩ ለአብርሃም የሰጠውን ቅዱስ ቃል ኪዳን አሰበ። ስለዚህ የተመረጠውን ሕዝቡን መርቶ አወጣ፤ እነርሱም በደስታ ዘመሩ፤ እልልም አሉ። የሌሎች ሕዝቦችን ምድር ሰጣቸው፤ ሌሎች የደከሙባቸውንም እርሻዎች አወረሳቸው። ይህንንም ሁሉ ማድረጉ ሕዝቡ ድንጋጌውን እንዲጠብቁና ሕጉንም እንዲፈጽሙ ነው።
መዝሙር 105:1-45 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ድንቅ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ክበሩ፥ ጌታን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። ጌታንና ኃይሉን ፈልጉ፥ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። አገልጋዮቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራውን ድንቅ ሥር አስቡ፥ ተአምራቱን የተናገረውንም ፍርድ። እርሱ ጌታ አምላካችን ነው፥ ፍርዱ በምድር ሁሉ ላይ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፥ ለይስሐቅም የማለውን፥ ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን፥ ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፥ እንዲህም አለ፦ ለአንተ የከነዓንን ምድር የተመደበላችሁን ርስታችሁን እሰጣለሁ፥ ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር አነስተኛና፥ ለሀገሩም እንግዶች በነበሩበት ጊዜ ነው። ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። የቀባኋቸውን አትንኩ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ። በፊታቸው ሰውን ላከ፥ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ። እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የጌታ ቃል ፈተነው። ንጉሥ ላከና ፈታው፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው። የቤቱ ጌታ፥ የንብረቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥ መኰንኖቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ። ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በአገልጋዮቹም ላይ ተንኰል ይፈጽሙ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። አገልጋዩን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ። ተኣምራቱን በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረጉ። ጨለማን ላከ፥ ጨለመባቸውም፥ በቃሉም ዐመፁ። ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። ምድራቸውና የንጉሦቻቸው ቤቶች በእንቁራሪት ተሞሉ። ተናገረ፥ የዝንብ መንጋና ተናካሽ ትንኞች በዳርቻቸው መጡ። ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ በምድራቸውም የእሳት ነበልባል ወረደ። ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥ የአገራቸውንም ተክሎች ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ። የአገራቸውንም በኩር ሁሉ፥ የጉልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ። ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ የተደናቀፈ አልነበረም። ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት። ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት እንዲያበራላቸው። ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈለቀ፥ ወንዞች በበረሃ ፈሰሱ፥ ለአገልጋዩ ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስታውሶአልና። ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ። የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ ከሕዝቦችም ድካም ወረሱ፥ ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ።