መዝሙር 10:12-18
መዝሙር 10:12-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ አምላክ ሆይ፤ ክንድህን አንሣ፤ ረዳት የሌላቸውንም አትርሳ። ክፉ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ለምን ክፉ ይናገራል? በልቡስ፣ “ስለ ሥራዬ አይጠይቀኝም” ለምን ይላል? አንተ ግን መከራንና ሐዘንን ታያለህ፤ በእጅህም ዋጋ ለመክፈል ትመለከታለህ፤ ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤ ለድኻ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ። የክፉውንና የበደለኛውን ክንድ ስበር፤ የእጁንም ስጠው፤ ምንም እስከማይገኝ ድረስ። እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤ ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ የተገፉትን ምኞት ትሰማለህ፤ ልባቸውን ታበረታለህ፤ ጆሮህንም ወደ እነርሱ ጣል ታደርጋለህ፤ ከዐፈር የተፈጠረ ሰው ከእንግዲህ እንዳያስጨንቃቸው፣ አንተ ለድኻ አደጉና ለተገፋው ትሟገታለህ።
መዝሙር 10:12-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ፥ ተነሥ! አምላክ ሆይ፥ ኀያል ክንድህን አንሣ! የተጨቈኑትንም ችላ አትበላቸው። ክፉ ሰዎች ለምን አያከብሩህም? ለምንስ በልባቸው “እግዚአብሔር አይቀጣንም” ይላሉ? አምላክ ሆይ! አንተ ግን ችግርንና ጭንቀትን አይተህ ልታስወግዳቸው መፍትሔ ታዘጋጃለህ፤ ችግረኛ ራሱን ለአንተ ይሰጣል፤ አንተም የሙት ልጆችን ትረዳለህ። የኃጢአተኞችንና የክፉ ሰዎችን ኀይል አድክም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ክፋትን እንዳያደርጉ በክፉ ሥራቸው ሁሉ ቅጣቸው። እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤ ለሌሎች አማልክት የሚሰግዱ ሕዝቦች ግን ከምድሩ ይጠፋሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምስኪኖችን ጸሎት ትሰማለህ፤ ልመናቸውንም አድምጠህ ታበረታታቸዋለህ። በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሌሎችን ለማስፈራራት እንዳይችል፥ አንተ ለወላጅ አልባና ለተጨቈኑ ሰዎች ትከላከላለህ።
መዝሙር 10:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህንም ከፍ ከፍ አድርግ፥ ድሆችን አትርሳ። ክፉ ስለምን እግዚአብሔርን ናቀ? በልቡም፦ “ፈልጎ አያገኘኝም” ይላልና። አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቁጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፥ ምስኪን እራሱን ለአንተ አሳልፎ ይሰጣል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ። የክፉዉንና የግፈኛውን ክንድ ሰባብር፥ ምንም እስከማይገኝ ድረስ ክፋቱን ፈልገህ አግኝ። ጌታ ለዘለዓለም ንጉሥ ነው፥ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ። ጌታ ሆይ የምስኪኖችን ምኞት ሰማህ፥ ልባቸውንም ታጸናለህ፥ ጆሮህንም ታዘነብላለህ፤ ፍርዱ ለወላጅ አልባና ለተጨቆነ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ ማሸበራቸውን እንዳይቀጥሉ።