መዝሙር 1:1-6
መዝሙር 1:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ምስጉን ነው፥ በዝንጉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኀጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ሰው። የእግዚአብሔር ሕግ ብቻ ፈቃዱ የሆነ፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ፥ እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ኃጥኣን እንዲህ አይደሉም፥ እንዲህ አይደሉም። ነገር ግን ነፋስ ከገጸ ምድር ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ዝንጉዎች በፍርድ፥ ኃጥኣንም በጻድቃን ምክር አይቆሙም። እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የኃጥኣን መንገድ ግን ትጠፋለች።
መዝሙር 1:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤ ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ፊት፣ ኀጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር መቆም አይችሉም። እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ይጠብቃልና፤ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።
መዝሙር 1:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በክፉ ሰዎች ምክር የማይሄድ፥ የኃጢአተኞችን መንገድ የማይከተል፥ ከፌዘኞች ጋር ኅብረት የማያደርግ የተባረከ ነው። እንዲህ ያለው ሰው፥ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ቀንና ሌሊትም ያሰላስለዋል። እርሱም፦ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፥ ቅጠሏም እንደማይረግፍ፥ በፈሳሽ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሥራ ሁሉ ይሳካለታል። ክፉዎች ግን እንደዚህ አይደሉም፤ እነርሱ ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ገለባ ናቸው። ስለዚህ ክፉ ሰዎች በፍርድ ቀን ከፍርድ አይድኑም፤ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ጉባኤ አይገኙም። ስለዚህ እግዚአብሔር የጻድቃንን አካሄድ ያውቃል፤ የክፉ ሰዎች አካሄድ ግን የሚያመራው ወደ ጥፋት ነው።
መዝሙር 1:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ብፁዕ ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በፌዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በጌታ ሕግ ደስ የሚለው፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለ፥ ፍሬውን በየጊዜው እንደሚሰጥ፥ ቅጠሉም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፥ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም። ጌታ የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።