ምሳሌ 30:18-33

ምሳሌ 30:18-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“እጅግ የሚያስደንቁኝ ሦስት ነገሮች አሉ፤ የማላስተውላቸውም አራት ናቸው፤ የንስር መንገድ በሰማይ፣ የእባብ መንገድ በቋጥኝ፣ የመርከብ መንገድ በባሕር፣ የሰውም መንገድ ከሴት ልጅ ጋራ ናቸው። “የአመንዝራዪቱ መንገድ ይህ ነው፤ በልታ አፏን በማበስ፣ ‘ምንም የሠራሁት ጥፋት የለም’ ትላለች። “ምድር በሦስት ነገር ትናወጣለች፤ እንዲያውም መሸከም የማትችላቸው አራት ነገሮች ናቸው፤ ባሪያ ሲነግሥ፣ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ፣ የተጠላች ሴት ባል ስታገባ፣ ሴት ባሪያ በእመቤቷ እግር ስትተካ። “በምድር ላይ አራት ነገሮች ትንንሽ ናቸው፤ ሆኖም እጅግ ጠቢባን ናቸው፤ ጕንዳኖች ደካማ ፍጥረታት ናቸው፤ ሆኖም ምግባቸውን በበጋ ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች ዐቅመ ደካማ ናቸው፤ ሆኖም መኖሪያቸውን በቋጥኞች መካከል ይሠራሉ፤ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ሆኖም ቅደም ተከተል ይዘው ይጓዛሉ፤ እንሽላሊት በእጅ ትያዛለች፤ ሆኖም በቤተ መንግሥት ትገኛለች። “አረማመዳቸው ግርማዊ የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም በሞገስ የሚጐማለሉ አራት ናቸው፤ ከአራዊት መካከል ኀይለኛ የሆነው፣ ከምንም ነገር ፊት ግንባሩን የማያጥፈው አንበሳ፤ ጐርደድ ጐርደድ የሚል አውራ ዶሮ፣ አውራ ፍየል፣ እንዲሁም በሰራዊቱ የታጀበ ንጉሥ ናቸው። “ተላላ ሆነህ ራስህን ከፍ ከፍ ካደረግህ፣ ወይም ክፉ ነገር ካቀድህ፣ እጅህን በአፍህ ላይ አድርግ። ወተት ሲናጥ ቅቤ እንደሚወጣው፣ አፍንጫን ሲያሹት እንደሚደማ፣ ቍጣን ማነሣሣትም ጥልን ይፈጥራል።”

ምሳሌ 30:18-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ላስተውላቸው የማልችል እጅግ ምሥጢር የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው። እነርሱም፦ “በሰማይ የሚበር ንስር፥ በአለት ላይ የሚጐተት እባብ፥ በባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብና ከሴት ጋር ፍቅር የያዘው ወንድ” ናቸው። የማትታመን ሚስት ሁኔታም እንዲሁ ነው፤ እርስዋ በባልዋ ላይ ታመነዝርና ንጹሕ ሰው በመምሰል “ምንም በደል አልፈጸምኩም” ትላለች። በሦስት ነገሮች ምክንያት ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ልትታገሥም አትችልም፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም “ባሪያ ሲነግሥ፥ ቦዘኔ ሲጠግብ፥ የተጠላች ሴት ባል ስታገባና፥ ሴት ባሪያ እመቤትዋን ስትወርስ” የሚከሠቱ ሁኔታዎች ናቸው። በዓለም ላይ በብልኅነታቸው የታወቁ አራት ትንንሽ ፍጥረቶች አሉ፤ ጒንዳኖች፦ ጒንዳኖች ደካሞች ናቸው፤ ነገር ግን በበጋ ጊዜ ምግባቸውን ያከማቻሉ። ሽኮኮዎች፦ ሽኮኮዎች ብርቱዎች አይደሉም፤ ነገር ግን መኖሪያቸውን በአለቶች መካከል ይሠራሉ። አንበጦች፦ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤ ነገር ግን ሁሉም በሥነ ሥርዓት ይጓዛሉ። እንሽላሊቶች፦ እንሽላሊቶች በእጅ ስለሚያዙ ቀላል ፍጥረቶች መስለው ቢታዩም፥ በቤተ መንግሥት እንኳ ሳይቀር በሁሉ ስፍራ ይገኛሉ። አረማመዳቸው አስደሳች የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ እነርሱም፥ በእንስሶች መካከል ብርቱ የሆኑና ከማንም ፊት የማይሸሹ አንበሶች፥ አውራ ፍየሎች፥ የሚንጐራደዱ አውራ ዶሮዎች፥ በሕዝቦቻቸው ፊት በክብር የሚታዩ ነገሥታት ናቸው። ሞኝነትህ ትምክሕተኛ እንድትሆን ቢያደርግህና ክፉ ነገር ለማድረግ ብታቅድ፥ ቆም ብለህ አስብ። ወተት ቢናጥ ቅቤ ያስገኛል፤ የሰው አፍንጫ ቢጠመዘዝ ይደማል፤ ቊጣ ቢነሣሣ ጠብን ያመጣል።

ምሳሌ 30:18-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም። እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው። የአመንዝራ ሴት መንገድም እንዲሁ ነው። በልታ አፍዋን የምታብስ፦ “አንዳች ክፉ ነገርም አላደረግሁም” የምትል። በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም። አገልጋይ በነገሠ ጊዜ፥ ሞኝ እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥ የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት አገልጋይም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ። በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፥ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፥ ገብረ ጉንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ። ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ። አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸውም ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ። እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል። መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፥ የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ ማንንም ፈርቶ የማይመለስ፥ በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፥ መንጋን የሚመራ አውራ ፍየል፥ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ። ከፍ ከፍ በማለት የተሞኝህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን። ወተት መናጥ ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣል፥ እንዲሁም ቁጣን መጐተት ጠብን ያመጣል።