ምሳሌ 3:21-26
ምሳሌ 3:21-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ፥ ቸል አትበል ዐሳቤንና ምክሬን ጠብቅ፤ ነፍስህ ትድን ዘንድ፥ ለአንገትህም ሞገስ ይሆንህ ዘንድ። ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንልሃል። በመንገድህም ሁሉ በመተማመን ትሄዳለህ፥ እግሮችህም አይሰነካከሉም። በተቀመጥህም ጊዜ አትፈራም፤ ብትተኛም መልካም እንቅልፍ ትተኛለህ። ከሚመጣብህም አስደንጋጭ ነገር፥ ከሚመጣውም የክፉዎች ሰዎች አደጋ አትፈራም፤ እግዚአብሔር በመንገድህ ሁሉ ይኖራልና፥ እግሮችህም እንዳይነዋወጡ ያቆማቸዋልና።
ምሳሌ 3:21-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ጥበብና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። ከዚያም መንገድህን ያለ ሥጋት ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም፤ ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።
ምሳሌ 3:21-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! መልካም ጥበብንና አርቆ ማስተዋልን አጥብቀህ ያዝ፤ ከአንተም እንዲርቁ አታድርግ። እነርሱም ለአንተ ረጅምና የአማረ ሕይወትን ይሰጡሃል። በመንገድህ ያለ ፍርሀት ተማምነህ መሄድ ትችላለህ፤ ከቶም አትሰናከልም። በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ሌሊቱንም ሙሉ የሰላም እንቅልፍ ታገኛለህ። በክፉ ሰዎች ላይ በድንገት የሚደርስ አደጋና ጥፋት ይደርስብኛል ብለህ አትፍራ። እግዚአብሔር መታመኛህ ሆኖ በወጥመድም ከመያዝ ይጠብቅሃል።
ምሳሌ 3:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥ ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥ ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።