ምሳሌ 2:1-6
ምሳሌ 2:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን ትሰማለች፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ልብህንም ልጅህን ለመምከር ታቀርባለህ፥ ጥበብን ብትጠራት፥ ቃልህንም ለማስተዋል ብትሰጥ፥ ዕውቀትንም በታላቅ ቃል ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ አምላክን ማወቅንም ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከፊቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤
ምሳሌ 2:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣ ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣ እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣ በዚያ ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።
ምሳሌ 2:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! የማስተምርህን ተቀበል፤ ትእዛዞቼንም በልብህ አኑር። የጥበብን ቃል አድምጥ፤ በጥንቃቄም አስተውለው። ማስተዋልን ጥራ፤ ለዕውቀትም ድምፅህን ከፍ አድርግ። ብር ወይም የተሰወረ ሀብት ለማግኘት ጥረት የምታደርገውን ያኽል ተግተህ ጥበብን ፈልጋት። ይህን ሁሉ ብታደርግ እግዚአብሔርን መፍራት ምን እንደ ሆነ ታውቃለህ፤ የአምላክንም ዕውቀት ታገኛለህ። ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ዕውቀትና ማስተዋልም የሚገኙት ከእርሱ ዘንድ ነው።
ምሳሌ 2:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ማመዛዘንን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እንደ ተደበቀ ዕንቁም ብትሻት፥ የዚያን ጊዜ ጌታን መፍራትን ትገነዘባለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። ጌታ ጥበብን ይሰጣልና፥ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፥