ምሳሌ 2:1-15

ምሳሌ 2:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን ትሰማለች፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ልብህንም ልጅህን ለመምከር ታቀርባለህ፥ ጥበብን ብትጠራት፥ ቃልህንም ለማስተዋል ብትሰጥ፥ ዕውቀትንም በታላቅ ቃል ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ አምላክን ማወቅንም ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከፊቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ እርሱ ቅንነትን ለሚያደርጉ ደኅንነትን ያከማቻል፤ በመንገዳቸውም ይቆምላቸዋል። የጽድቅን ጎዳና ይጠብቃል፤ የሚፈሩትንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ታውቃለህ፤ መልካም መንገድንም ሁሉ ታቃናለህ። ጥበብ ወደ ልብህ በመጣች ጊዜ፥ ዕውቀትም ለነፍስህ መልካምና ክብር በሆነች ጊዜ፥ መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤ የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች። አንተን ከክፉ መንገድ፥ ምንም የሚታመን ነገርን ከማይናገር ሰውም ታድንህ ዘንድ፥ እነርሱ በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና ለሚተዉ፥ ክፉ በመሥራት ደስ ለሚላቸው ክፋትንም በመመለስ ሐሤትን ለሚያደርጉ፥ መንገዳቸው ጐጻጕጽ፥ አካሄዳቸው ጠማማ ለሆኑ ወዮላቸው!

ምሳሌ 2:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣ ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣ እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣ በዚያ ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል። እርሱ ለቅኖች ትክክለኛ ጥበብ ያከማቻል፤ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ይሆናቸዋል፤ የፍትሕን መንገድ ይጠብቃል፤ የታማኞቹንም አካሄድ ያጸናል። በዚያ ጊዜ ጽድቅን፣ ፍትሕን፣ ሚዛናዊነትን፣ መልካሙንም መንገድ ሁሉ ትገነዘባለህ፤ ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤ የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል። ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤ እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፣ ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው፣ በክፋት ጐዳና ሐሤት የሚያደርጉ፣ መንገዳቸው ጠማማ፣ በአካሄዳቸው ጠመዝማዞች ናቸው።

ምሳሌ 2:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ልጄ ሆይ! የማስተምርህን ተቀበል፤ ትእዛዞቼንም በልብህ አኑር። የጥበብን ቃል አድምጥ፤ በጥንቃቄም አስተውለው። ማስተዋልን ጥራ፤ ለዕውቀትም ድምፅህን ከፍ አድርግ። ብር ወይም የተሰወረ ሀብት ለማግኘት ጥረት የምታደርገውን ያኽል ተግተህ ጥበብን ፈልጋት። ይህን ሁሉ ብታደርግ እግዚአብሔርን መፍራት ምን እንደ ሆነ ታውቃለህ፤ የአምላክንም ዕውቀት ታገኛለህ። ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ዕውቀትና ማስተዋልም የሚገኙት ከእርሱ ዘንድ ነው። እርሱ ለቀጥተኞች መልካም ጥበብን ይሰጣል፤ በተግባራቸው ነቀፋ ለሌለባቸው ጋሻቸው ነው። የፍትሕን ሂደት ይከታተላል፤ በታማኝነት የሚያገለግሉትንም ይጠብቃል። እኔ የምልህን ሁሉ ብትሰማ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክልና ቅን የሆነውን መንገድ ትገነዘባለህ፤ ልታደርገው የሚገባህንም መልካም ነገር ሁሉ ታውቃለህ። ጠቢብ ትሆናለህ፤ ዕውቀትም ደስታን ይሰጥሃል። አርቆ ማስተዋል ይጠብቅሃል፤ መገንዘብም ከክፉ ነገር ይከላከልልሃል። ጥበብ ከክፉ ሰዎች መንገድና ከጠማማ ንግግራቸው ያድንሃል። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ለመኖር የጽድቅን መንገድ የተዉ ናቸው። እነርሱን ደስ የሚያሰኛቸው ቀናውን ነገር ማጣመምና ተንኰል የተሞላበት ክፉ ሥራ መሥራት ነው። እነርሱ እምነት የማይጣልባቸውና ጠማሞች ናቸው።

ምሳሌ 2:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ማመዛዘንን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እንደ ተደበቀ ዕንቁም ብትሻት፥ የዚያን ጊዜ ጌታን መፍራትን ትገነዘባለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። ጌታ ጥበብን ይሰጣልና፥ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፥ እርሱ ለቅኖች ስምረትን ያከማቻል፥ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፥ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፥ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ። ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፥ ማመዛዘን ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይከላከልልሃል፥ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፥ እነርሱም በጨለማ መንገድ ለመሄድ የቀናውን ጎዳና የሚተዉ፥ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ሐሤትን የሚያደርጉ፥ መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፥