ምሳሌ 18:13-24 - Compare All Versions
ምሳሌ 18:13-24 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል። በሕመም ጊዜ፣ ሰውን መንፈሱ ትደግፈዋለች፤ የተሰበረውን መንፈስ ግን ማን ሊሸከም ይችላል? የአስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይገበያል፤ የጠቢብም ጆሮ አጥብቆ ይሻታል። እጅ መንሻ ለሰጪው መንገድ ትከፍትለታለች፤ ታላላቅ ሰዎች ፊትም ታቀርበዋለች። አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው። ዕጣ መጣጣል ሙግትን ያስቆማል፤ ኀይለኛ ባላንጣዎችንም ይገላግላል። የተበደለ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤ ጠቡም እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ ነው። ሰው በአንደበቱ ፍሬ ሆዱ ይጠግባል፤ በከንፈሩም ምርት ይረካል። አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት፤ የሚወድዷትም ፍሬዋን ይበላሉ። ሚስት የሚያገኝ መልካም ነገርን ያገኛል፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል። ድኻ በመለማመጥ ምሕረት ይለምናል፤ ሀብታም ግን በማናለብኝነት ይመልሳል። ወዳጅ የሚያበዛ ሰው ራሱን ለጥፋት ይዳርጋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።
ምሳሌ 18:13-24 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ሳያዳምጡ መልስ መስጠት፥ ሞኝ ያደርጋል፤ አሳፋሪም ነው። ጠንካራ መንፈስ ሕመምን ያስታግሣል፤ መንፈሱ የደከመውን ግን ማንም አይረዳውም። የጥበበኛ ሰው ልብ ዕውቀትን ገንዘብ ያደርጋል፤ የአስተዋዮችም ጆሮ ጥበብን ይፈልጋል። ስጦታ ለሰጪው መንገድን ይከፍትለታል፤ ወደ ትልልቆች ሰዎችም ፊት መቅረብ ያስችለዋል። በአደባባይ በመጀመሪያ ቀርቦ የሚናገር ሰው ተከራካሪው መጥቶ ጥያቄ እስከሚያቀርብለት ድረስ፥ ዘወትር እርሱ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስለዋል። ዕጣ መጣል ጠብን ያበርዳል፤ ሁለት ጠንካራ ተከራካሪዎችንም ይገላግላል። ወንድምህን እርዳው፤ እርሱም በከተማ ዙሪያ እንዳለ ጠንካራ ግንብ ይጠብቅሃል፤ ከእርሱ ጋር ብትጣላ ግን በሩን ይዘጋብሃል። ሰው በሚናገረው የንግግር ውጤት በመርካት ተደስቶ ይኖራል። አንደበትህ ሕይወትህን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል፤ ስለዚህ በአንደበትህ ወዳጆችን ብታፈራ ተደስተህ ትኖራለህ። ሚስት ከእግዚአብሔር የምትሰጥ በረከት ስለ ሆነች ሚስት ካገኘህ መልካም ነገር አግኝተሃል ማለት ነው፤ ድኻ እየተለማመጠ በትሕትና ይናገራል፤ ሀብታም ግን በትምክሕት ይመልሳል። ወዳጆች ሳይሆኑ ወዳጆች መስለው የሚታዩ አሉ፤ እውነተኛ ወዳጅ ግን ከወንድም ይበልጣል።
ምሳሌ 18:13-24 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል። የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፥ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል? የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች። የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች። ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፥ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል። ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥ በኃያላንም መካከል ትበይናለች። የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፥ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው። የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል፥ ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል። ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፥ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ። ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከጌታም ሞገስን ይቀበላል። ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፥ ሀብታም ግን በድፍረት ይመልሳል። ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፥ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።