ምሳሌ 13:1-25 - Compare All Versions

ምሳሌ 13:1-25 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ጠቢብ ልጅ የአባቱን ምክር በማስተዋል ይሰማል፤ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አያዳምጥም። ሰው ከከንፈሩ ፍሬ መልካም ነገር ያገኛል፤ ወስላቶች ግን ዐመፅን ይናፍቃሉ። አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤ አፉ እንዳመጣለት የሚናገር ግን ይጠፋል። ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤ የትጉሆች ምኞት ግን ይረካል። ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ክፉ ሰው ግን ኀፍረትንና ውርደትን ያመጣል። ጽድቅ ቅን የሆነውን ሰው ትጠብቀዋለች፤ ክፋት ግን ኀጢአተኛውን ትጥለዋለች። ምንም ሳይኖረው ባለጠጋ መስሎ የሚታይ ሰው አለ፤ ሌላው ድኻ መስሎ ይታያል፤ ግን ብዙ ሀብት አለው። የሰው ሀብቱ ለሕይወቱ ቤዛ ሊሆነው ይችላል፤ ድኻው ግን ሥጋት የለበትም። የጻድቃን ብርሃን ደምቆ ይበራል፤ የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል። ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች። ያላግባብ የተገኘ ገንዘብ እየተመናመነ ያልቃል፤ ገንዘቡን ጥቂት በጥቂት የሚያከማች ግን ይጠራቀምለታል። ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል፤ የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው። ምክርን የሚያቃልል በራሱ ላይ ጥፋት ያመጣል፤ ትእዛዝን የሚያከብር ግን ወሮታን ይቀበላል። የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን ከሞት ወጥመድ ያድነዋል። መልካም ማስተዋል ሞገስን ታስገኛለች፤ የከዳተኞች መንገድ ግን አስቸጋሪ ነው። አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤ ሞኝ ግን ቂልነቱን ይገልጣል። ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል። ተግሣጽን የሚንቅ ወደ ድኽነትና ኀፍረት ይሄዳል፤ ዕርምትን የሚቀበል ሁሉ ግን ይከበራል። ምኞት ስትፈጸም ነፍስን ደስ ታሰኛለች፤ ሞኞች ግን ከክፋት መራቅን ይጸየፋሉ። ከጠቢብ ጋራ የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሞኝ ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል። መጥፎ ዕድል ኀጢአተኛን ይከታተላል፤ ብልጽግና ግን የጻድቃን ዋጋ ነው። ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ ውርስ ትቶ ያልፋል፤ የኀጢአተኞች ሀብት ግን ለጻድቃን ይከማቻል። የድኾች ዕርሻ የተትረፈረፈ ምርት ያስገኛል፤ የፍትሕ መጓደል ግን ጠራርጎ ይወስደዋል። በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወድደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል። ጻድቅ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ የክፉዎች ሆድ ግን እንደ ተራበ ይኖራል።

ምሳሌ 13:1-25 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ብልኅ ልጅ የአባቱን ምክር ይቀበላል፤ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም። ደጋግ ሰዎች የመልካም አነጋገራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ የአታላዮች ምኞት ግን የግፍ ሥራ ለመፈጸም ነው። ተጠንቅቆ የሚናገር ሕይወቱን ይጠብቃል። ግዴለሽ ተናጋሪ ግን ጥፋት ይደርስበታል። ሰነፍ አንድ ነገር ለማግኘት አጥብቆ ይመኛል፤ ይሁን እንጂ አያገኝም፤ ትጉህ ሠራተኛ ግን የሚፈልገውን ሁሉ ያገኛል። ደጋግ ሰዎች ሐሰትን ይጠላሉ፤ የክፉዎች ሰዎች ንግግር ግን አሳፋሪና አስነዋሪ ነው። ደጋግ ሰዎች ደግነታቸው ይጠብቃቸዋል፤ ኃጢአተኞችን ግን ኃጢአታቸው ያጠፋቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ምንም ሳይኖራቸው ሀብታም መስለው ለመታየት ይጥራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ ሀብት እያላቸው፥ ምንም ሀብት እንደሌላቸው መስለው ይኖራሉ። ሀብታም በገንዘብ ሕይወቱን ለማዳን ይጣጣራል፤ ድኻ ግን የሚወሰድበት ሀብት ስለሌለው አይጨነቅም። የጻድቃን ብርሃን ያንጸባርቃል፤ የኃጢአተኞች መብራት ግን ይጠፋል። ትዕቢት ጠብን ያመጣል፤ ምክርን መጠየቅ ግን ብልኅነት ነው። ያለ ድካም በቀላሉ የተገኘ ሀብት ወዲያው ይጠፋል፤ ተግቶ በመሥራት የተገኘ ሀብት ግን እየበዛ ይሄዳል። ተስፋ ሲዘገይ ልብን ያሳዝናል፤ የተመኙት ነገር ሲፈጸም ግን ደስ ያሰኛል። መልካም ምክርን የሚንቅ ችግር ይደርስበታል፤ ትእዛዝን የሚያከብር ግን ዋጋ ያገኝበታል። የጠቢባን ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሕይወትህ በአደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ እንድታመልጥ ይረዳሃል። አስተዋይ መሆን ያስከብራል፤ ከዳተኛነት ግን ወደ ጥፋት ያደርሳል። አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን አላዋቂነታቸውን ይገልጣሉ። ክፉ መልእክተኛ ችግርን ያመጣል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ሰላምን ያስገኛል። ትምህርት የማይወድ ሰው፥ ድኽነትና ውርደት ይገጥመዋል፤ ተግሣጽን የሚቀበል ግን ይከበራል። የተመኙትን ነገር ማግኘት እጅግ ደስ ያሰኛል፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን ከክፉ ነገር መራቅ አይፈልጉም። ከጥበበኞች የሚወዳጅ ጥበበኛ ይሆናል። ማስተዋል ከጐደላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን ይጐዳል። ኃጢአተኞችን በሄዱበት ስፍራ ሁሉ መከራ ይከተላቸዋል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ የሚተላለፍ ሀብት ያገኛል፤ የኃጢአተኞችን ሀብት ግን ቅን ሰዎች ይወርሱታል። የድኻ እርሻ የተትረፈረፈ ምርትን ሊያስገኝ ይችል ይሆናል። ከፍርድ መጓደል የተነሣ ግን ይጠፋል። ልጁን የማይቀጣ አይወደውም ማለት ነው፤ ልጁን የሚወድ ግን ቀጥቶ ያሳድገዋል። እውነተኞች ሊበሉ የሚፈልጉትን ያኽል ያገኛሉ። ኃጢአተኞች ግን ዘወትር ይራባሉ።

ምሳሌ 13:1-25 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ዐዋቂ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል፤ የማይሰማ ልጅ ግን ይጠፋል። ደግ ሰው ከጽድቅ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዐመፀኞች ነፍሳት ግን በጨርቋነታቸው ይጠፋሉ። አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ በከንፈሩ የሚቸኩል ግን ራሱን ይጥላል። የማይሠራ ሁሉ በምኞት ይኖራል። የደጋጎች እጅ ግን ይተጋል። ጻድቅ የሐሰትን ቃል ይጠላል፤ ኀጢአተኛ ግን ያፍራል፥ ተገልጦም አይመጣም። መንገዳቸው ቀና የሆነውን የዋሃንን ጽድቅ ትጠብቃቸዋለች፤ ኀጢአተኞችን ግን ኀጢአታቸው በደለኛ ታደርጋቸዋለች። ምንም ሳይኖራቸው ራሳቸውን ባለጠጎች የሚያደርጉ አሉ፥ ባለጠግነታቸው ብዙ ሲሆን ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉም አሉ። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሃ ግን ቍጣን አይቃወምም። ለጻድቃን ሁልጊዜ ብርሃን ነው፤ የኃጥኣን መብራት ግን ትጠፋለች። የሐሰተኞች ነፍሳት በኀጢአት ይስታሉ። ጻድቃን ግን ይራራሉ፥ ይመጸውታሉም። ክፉ ሰው ከመሳደብ ጋር ክፋትን ይሠራል፤ ራሳቸውን የሚያውቁ ግን ብልሆች ናቸው። በኀጢአት በችኮላ የሚገኝ ሀብት ይጐድላል፥ በእውነት ለራሱ የሚሰበስብ ግን ይበዛለታል። ጻድቅ ይራራል፥ ያበድራልም። ከሚበለጽግና በተስፋ ከሚቈይ ሰውነቱን ሊረዳ የሚጀምር ይሻላል። መልካም ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ናት። የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያቃልለውን እርሱ ያቃልለዋል፥ ትእዛዙን የሚሰማ ግን በእርሱ በሕይወት ይኖራል። ለውሸተኛ ልጅ ምንም ደግነት የለም፥ ለብልህ አገልጋይ ግን ሥራው መልካም ይሆናል። መንገዱም ይቃናል። የብልህ ሰው ሕግ የሕይወት ምንጭ ነው። ማስተዋል የሌለው ግን በኀጢአት ይሞታል። መልካም ዕውቀት ሞገስንና ጥበብን ይሰጣል፤ የቸለልተኞች መንገድ ግን በጥፋት ውስጥ ነው። ብልህ ሁሉ በዕውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ክፋቱን ይገልጣል። ሰነፍ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ ብልህ መልእክተኛ ግን ራሱን ያድናል። ትምህርት ድህነትንና ጕስቍልናን ያስወግዳል፤ ተግሣጽን የሚጠብቅ ግን ይከብራል። የደጋግ ሰዎች ምኞት ነፍስን ያድናል፤ የሰነፎች ሥራ ግን ከዕውቀት የራቀ ነው። ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ ከአላዋቂዎች ጋር የሚሄድ ግን አላዋቂ ይሆናል። በደለኞችን ክፉ ነገር ይከተላቸዋል፤ ጻድቃንን ግን መልካም ነገር ያገኛቸዋል። ደግ ሰው ለልጅ ልጅ ያወርሳል፥ የኀጢአተኞች ብልጽግና ግን ለጻድቃን ይደልባል። ጻድቃን ለብዙ ዓመት በብልጽግና ይኖራሉ፤ ዐመፀኞች ግን ፈጥነው ይጠፋሉ። በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድድ ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል። ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፤ የኃጥኣን ሰውነት ግን ትቸገራለች።

ምሳሌ 13:1-25 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል፥ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም። ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፥ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች። አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፥ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋት ያገኘዋል። የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፥ አንዳችም አታገኝም፥ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች። ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፥ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም። በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፥ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል። ራሱን ሀብታም የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፥ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፥ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም። ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፥ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል። በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፥ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት። በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፥ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፥ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት። ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፥ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል። ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው። መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፥ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት። ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፥ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል። መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፥ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው። ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፥ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል። የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፥ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ። ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፥ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፥ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ። ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፥ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች። በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፥ ከፍርድ መጉደል የተነሣ ግን ይጠፋል። በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፥ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጸዋል። ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፥ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል።