ምሳሌ 12:17-22
ምሳሌ 12:17-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጻድቅ ሰው የተገለጠ እውነትን ያስተምራል፤ የክፉዎች ምስክርነት ግን ውሸት ነው። በሐሰት የሚመሰክሩ በሰይፍ ይገድላሉ፤ በአፋቸው ሰይፍ አለና። የጠቢባን ምላስ ግን የቈሰለውን ይፈውሳል። የጻድቃን ከንፈሮች ምስክርነትን ያቀናሉ፥ የሚቸኩል ምስክር ግን ክፉ አንደበት አለው። ክፉን በሚያስብ ልብ ውስጥ ማታለል አለ፤ ሰላምን የሚወዱ ግን ደስ ይላቸዋል፥ ጻድቅን ምንም ክፉ ነገር ደስ አያሰኘውም፤ ክፉዎች ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ሐሰተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።
ምሳሌ 12:17-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል። ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል። እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው። ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤ ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል።
ምሳሌ 12:17-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እውነትን የሚናገር ሁሉ የታመነ ምስክርነትን ይሰጣል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ሰውን ያታልላል። ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቈስላል፤ በጥበብ የተነገረ ቃል ግን ይፈውሳል። እውነት ግን ጸንታ ትኖራለች። ሐሰት ዘላቂነት የለውም፤ ክፋትን በሚያቅዱ ሰዎች ልብ ተንኰል አለ፤ ሰላም የሚገኝበትን ነገር የሚመክሩ ግን ደስታን ያገኛሉ። ደጋግ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አይገጥማቸውም፤ ክፉዎች ግን መከራ ይበዛባቸዋል። የሚያተርፉት ነገር የለም። እግዚአብሔር ሐሰተኛ አንደበትን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ይደሰታል።
ምሳሌ 12:17-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።