ፊልጵስዩስ 4:1-5
ፊልጵስዩስ 4:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም የተወደዳችሁና የምናፍቃችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ደስታችንና አክሊላችን ናችሁ፤ ወዳጆቻችን ሆይ፥ እንዲህ ቁሙ፤ በጌታችንም ጽኑ። ኤዎድያና ስንጣክን ሆይ፥ በአንድ ልብ ጌታችንን ለማገልገል ታስቡ ዘንድ እማልዳችኋለሁ። ወንድሜና አጋዤ ስትሪካ ሆይ፥ እንድትረዳቸው አንተንም እለምንሃለሁ፤ ወንጌልን በማስተማር ከቀሌምንጦስና ሥራቸው ከተባበረ፥ ስማቸውም በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፈላቸው ከወንድሞቻችንም ሁሉ ጋር ከእኔም ጋር ደክመዋልና። ዘወትር በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላችኋለሁ፦ ደስ ይበላችሁ። ፍጹምነታችሁም በሰው ሁሉ ዘንድ ይታወቅ። እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤
ፊልጵስዩስ 4:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ የምወድዳችሁና የምናፍቃችሁ፣ ወንድሞቼ ደስታዬና አክሊሌ የሆናችሁ፣ እንዲሁም ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ሁኔታ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ! በጌታ አንድ ሐሳብ እንዲኖራቸው ኤዎድያንን እለምናለሁ፤ ሲንጤኪንንም እለምናለሁ። አዎን፤ አንተ ታማኝ ባልደረባዬ ሆይ፤ ወንጌልን በማሠራጨት ረገድ ከእኔና ከቀሌምንጦስ ጋራ እንዲሁም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎች የሥራ ጓደኞቼ ጋራ የተጋደሉትን እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ! ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ቅርብ ነው።
ፊልጵስዩስ 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ። በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ።
ፊልጵስዩስ 4:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ የደስታዬና የሥራዬ አክሊል የሆናችሁ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ጸንታችሁ ኑሩ። ኤዎድያና ሲንጢኪ እርስ በርሳቸው በጌታ ተስማምተው እንዲኖሩ እለምናቸዋለሁ። አንተም እዚያ ያለኸው ታማኝ የሥራ ጓደኛዬ እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ፤ እነዚህ ሴቶች ከእኔ ጋር ከቀሌምንጦስና ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎችም የሥራ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ወንጌልን በማዳረስ ረገድ ተጋድለዋል። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜም “ደስ ይበላችሁ!” እላለሁ። ደግነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ተመልሶ ሊመጣ ቀርቦአል፤
ፊልጵስዩስ 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ደስታዬና አክሊሌ ናችሁ፤ የተወደዳችሁ ሆይ! በዚህ መንገድ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ። በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ! ከእኔ ጎን በመቆም ከቀለሜንጦስ ጋር አብረው በወንጌል ሥራ ተጋድለዋልና እነዚህን ሴቶችና የተቀሩትን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩትን እንድትረዱአቸው እለምንሃለሁ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፤ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ መምጫው ቀርቦአል።