ፊልጵስዩስ 3:15-21
ፊልጵስዩስ 3:15-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖርም፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደ ነበረበት ጊዜ ተጠባበቋቸው። ዘወትር እንደምነግራችሁ፥ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና፤ አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደ ሆኑ በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ። እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊዉንም የሚያስቡ ናቸው። እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት፤ ከዚያም እርሱን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን። እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋዉንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት ነው።
ፊልጵስዩስ 3:15-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እኛ ብስለት ያለን ሁላችን ነገሮችን በዚህ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፤ በአንዳንድ ነገር የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር እርሱንም ይገልጥላችኋል። ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፤ የእኔን አርኣያነት በመከተል ከሌሎች ጋራ ተባበሩ፤ እኛ በሰጠናችሁ ምሳሌነት መሠረት የሚኖሩትንም አስተውሉ። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደ ነገርኋችሁ፣ አሁንም እንደ ገና፣ ያውም በእንባ እነግራችኋለሁ፤ ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው በምድራዊ ነገር ላይ ነው። እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
ፊልጵስዩስ 3:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
ፊልጵስዩስ 3:15-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ በመንፈሳዊ ሕይወት የጠነከርን ሁሉ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፤ የምትለያዩበት ሐሳብ በመካከላችሁ ቢኖር ይህንንም ሐሳብ እግዚአብሔር ግልጥ ያደርግላችኋል። ያም ሆነ ይህ እስከ አሁን ከደረስንበት መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! የእኔን ምሳሌነት ለመከተል ተባበሩ፤ የእኛንም ምሳሌነት የሚከተሉትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ከአሁን በፊት ብዙ ጊዜ እንደ ነገርኳችሁና አሁንም እንባዬን እያፈሰስኩ እንደምነግራችሁ ሁሉ ብዙዎቹ በአካሄዳቸው የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነዋል። የእነርሱ አምላክ ሆዳቸው ነው፤ አሳፋሪ የሆነ ነገር ለእነርሱ ክብራቸው ነው፤ ሐሳባቸውም የሚያተኲረው በምድራዊ ነገር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእነርሱ መጨረሻ ጥፋት ነው። እኛ ግን የሰማይ መንግሥት ዜጎች ነን፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን። እርሱ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ የእርሱን ክቡር ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል፤ ይህንንም የሚያደርገው ሁሉን በሥልጣኑ ሥር ለማድረግ በሚያስችለው ኀይል ነው።
ፊልጵስዩስ 3:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ በአእምሮ የበሰልን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም ለእናንተ ምሳሌ እንደ ሆንን እንዲሁ የሚመላለሱትን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ ነገርኋችሁ፤ አሁንም እያነባሁ ስለ እነርሱ እነግራችኋለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ደግሞ ለራሱ ሁሉን ነገር በሥሩ ለማስገዛት በሚችልበት ኃይሉ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።