ፊልጵስዩስ 3:12-16
ፊልጵስዩስ 3:12-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ይህን ፈጽሜ የተቀበልሁ አይደለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ እኔን የመረጠበትን አገኝ ዘንድ እሮጣለሁ እንጂ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግን ፍጻሜዬን ገና ያገኘሁ አይመስለኝም። የኋላዬን እረሳለሁና፥ ወደ ፊቴም ፈጥኜ እገሠግሣለሁና፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን የጥሪ ዋጋ ለማግኘት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖርም፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ።
ፊልጵስዩስ 3:12-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። እንግዲህ እኛ ብስለት ያለን ሁላችን ነገሮችን በዚህ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፤ በአንዳንድ ነገር የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር እርሱንም ይገልጥላችኋል። ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።
ፊልጵስዩስ 3:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።
ፊልጵስዩስ 3:12-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህን ሁሉ ገና አላገኘሁም፤ ወይም በዚህ ሁሉ ፍጹም ሆኜአለሁ ለማለት አልችልም፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔን የእርሱ አድርጎ ያዘጋጀልኝን ሽልማት ለማግኘት ወደፊት በመሮጥ እተጋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ! ገና ወደዚያ እንደ ደረስኩ አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ይኸውም በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው። እንግዲህ በመንፈሳዊ ሕይወት የጠነከርን ሁሉ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፤ የምትለያዩበት ሐሳብ በመካከላችሁ ቢኖር ይህንንም ሐሳብ እግዚአብሔር ግልጥ ያደርግላችኋል። ያም ሆነ ይህ እስከ አሁን ከደረስንበት መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ይሁን።
ፊልጵስዩስ 3:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍጹም ለመሆን አልበቃሁም፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደ ፊት እሮጣለሁ። ወንድሞች ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደ ፊት እዘረጋለሁ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያለውን የመጠራት ሽልማት እንዳገኝ ወደ ግቡ እሮጣለሁ። እንግዲህ በአእምሮ የበሰልን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።