ፊልጵስዩስ 3:1-4
ፊልጵስዩስ 3:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ እኔም ስጽፍላችሁ ቸል አልልም፤ ያበረታችኋልና። ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉ አድራጊዎችም ተጠበቁ፤ ሥጋቸውን ብቻ በመቍረጥ ተገዝረናል ከሚሉም ተጠበቁ። ግዙራንስ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናገለግለውና የምናመልከው እኛ ነን፤ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ እንመካለን እንጂ በሥጋችን የምንመካ አይደለም። እኔም ግዝረት ሳለኝ በግዝረት አልመካም፤ በግዝረት መመካትን የሚያስብ ካለም እኔ እርሱን እበልጠዋለሁ።
ፊልጵስዩስ 3:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ! ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ፣ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል። ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ። እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና። ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ። ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤
ፊልጵስዩስ 3:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።
ፊልጵስዩስ 3:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጨረሻም ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ያንን ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁን ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አያሰለቸኝም፤ እናንተን ግን ከስሕተት ሊጠብቃችሁ ይችላል። እንደ ውሻ ከሚልከፈከፉ ከክፉ አድራጊዎች ተጠንቀቁ፤ ሥጋን ከሚቈራርጡ (ከሚገርዙ) ተጠንቀቁ። እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናመልክና በውጭ በሚታየው ሥርዓት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የምንመካ ስለ ሆንን በእውነት ተገርዘናል። ትምክሕት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ በብዙ ነገር ልመካ እችላለሁ፤ በውጭ በሚታየው ሥርዓት የሚመካ ሰው ቢኖር እኔ ከእርሱ ይበልጥ የምመካበት ብዙ ምክንያት አለኝ።
ፊልጵስዩስ 3:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ። ለእናንተ ተመሳሳይ የሆነን ነገር መልሼ ለመጻፍ ለእኔ አይታክተኝም፤ ይህ ለእናንተ ለደኅንነት የሆነ ነውና። ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፤ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን በእውነትም ከተገረዙት ወገን የሆንን ነንና። እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት ነገር ያለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።