ፊልጵስዩስ 3:1-21
ፊልጵስዩስ 3:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ እኔም ስጽፍላችሁ ቸል አልልም፤ ያበረታችኋልና። ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉ አድራጊዎችም ተጠበቁ፤ ሥጋቸውን ብቻ በመቍረጥ ተገዝረናል ከሚሉም ተጠበቁ። ግዙራንስ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናገለግለውና የምናመልከው እኛ ነን፤ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ እንመካለን እንጂ በሥጋችን የምንመካ አይደለም። እኔም ግዝረት ሳለኝ በግዝረት አልመካም፤ በግዝረት መመካትን የሚያስብ ካለም እኔ እርሱን እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገዘርሁ፥ ከእስራኤል ሕዝብ ከብንያም ነገድ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ በኦሪትም ፈሪሳዊ ነበርሁ። በኦሪት ጽድቅም ያለ ነውር ሆኜ በቅንዐት ምእመናንን አሳድድ ነበር። ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ያን ጥቅሜን ላጣው ወደድሁ። ክርስቶስን አገለግለው ዘንድ፥ ሁሉን የተውሁለት፥ እንደ ጕድፍም ያደረግሁለት የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ኀይልና ገናናነት ስለማውቅ ሁሉን እንደ ኢምንት ቈጠርሁት። በእርሱም እጸና ዘንድ፥ ዛሬ የኦሪት ጽድቅ ሳይኖረኝ ክርስቶስን በማመን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጽድቅ አለኝ እንጂ። በእርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን አውቀዋለሁ፤ የመነሣቱንም ኀይል በሕማሙ እሳተፈዋለሁ፤ በሞቱም እመስለዋለሁ። ይኸውም ሙታን በሚነሡ ጊዜ ምናልባት በዚህ አገኘው እንደ ሆነ ብዬ ነው። ነገር ግን ይህን ፈጽሜ የተቀበልሁ አይደለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ እኔን የመረጠበትን አገኝ ዘንድ እሮጣለሁ እንጂ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግን ፍጻሜዬን ገና ያገኘሁ አይመስለኝም። የኋላዬን እረሳለሁና፥ ወደ ፊቴም ፈጥኜ እገሠግሣለሁና፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን የጥሪ ዋጋ ለማግኘት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖርም፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደ ነበረበት ጊዜ ተጠባበቋቸው። ዘወትር እንደምነግራችሁ፥ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና፤ አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደ ሆኑ በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ። እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊዉንም የሚያስቡ ናቸው። እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት፤ ከዚያም እርሱን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን። እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋዉንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት ነው።
ፊልጵስዩስ 3:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ! ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ፣ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል። ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ። እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና። ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ። ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ዘር፣ ከብንያም ወገን የተወለድሁ ስሆን፣ ከዕብራውያንም ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ከተነሣ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅናት ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበርሁ፤ ሕግን በመፈጸም ስለሚገኝ ጽድቅ ከሆነም፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደ ጕድለት ቈጥሬዋለሁ። ከዚህም በላይ ለርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋራ ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ ሕግ በመጠበቅ የሚገኝ የራሴ ጽድቅ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ ከእምነትም በሆነ ጽድቅ በርሱ ዘንድ እንድገኝ ነው። ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤ ለሙታን ትንሣኤም እንድደርስ እናፍቃለሁ። ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። እንግዲህ እኛ ብስለት ያለን ሁላችን ነገሮችን በዚህ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፤ በአንዳንድ ነገር የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር እርሱንም ይገልጥላችኋል። ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፤ የእኔን አርኣያነት በመከተል ከሌሎች ጋራ ተባበሩ፤ እኛ በሰጠናችሁ ምሳሌነት መሠረት የሚኖሩትንም አስተውሉ። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደ ነገርኋችሁ፣ አሁንም እንደ ገና፣ ያውም በእንባ እነግራችኋለሁ፤ ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው በምድራዊ ነገር ላይ ነው። እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
ፊልጵስዩስ 3:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቍኦጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቍኦጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጕኦዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቍኦጥራለሁ፤ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
ፊልጵስዩስ 3:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጨረሻም ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ያንን ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁን ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አያሰለቸኝም፤ እናንተን ግን ከስሕተት ሊጠብቃችሁ ይችላል። እንደ ውሻ ከሚልከፈከፉ ከክፉ አድራጊዎች ተጠንቀቁ፤ ሥጋን ከሚቈራርጡ (ከሚገርዙ) ተጠንቀቁ። እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናመልክና በውጭ በሚታየው ሥርዓት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የምንመካ ስለ ሆንን በእውነት ተገርዘናል። ትምክሕት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ በብዙ ነገር ልመካ እችላለሁ፤ በውጭ በሚታየው ሥርዓት የሚመካ ሰው ቢኖር እኔ ከእርሱ ይበልጥ የምመካበት ብዙ ምክንያት አለኝ። እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዤአለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ነገድ የሆንኩ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም የተነሣ ጥርት ያልኩ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁድን ሕግ ስለ መጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበር። ስለ ኦሪት ሕግ በመቅናትም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን አማኞች አሳድ ነበር። ሕግን በመጠበቅ ስለ መጽደቅም ቢሆን ያለ ነቀፋ እኖር ነበርኩ። እንግዲህ ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው ከንቱ ነገሮች አድርጌ እቈጥራቸዋለሁ። ከዚህም በቀር ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ስለማምን ሁሉን ነገር እንደ ኪሣራ እቈጥረዋለሁ፤ ስለ እርሱም ሁሉን ነገር አጥቻለሁ። ክርስቶስንም ለማግኘት ስል ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቈጥራለሁ። ይህንንም የማደርግበት ምክንያት በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴን ጽድቅ ትቼ በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ በማመን ለማግኘትና ከእርሱም ጋር ለመሆን ነው። ሌላው ምክንያት ክርስቶስንና የክርስቶስን የትንሣኤ ኀይል ለማወቅ፥ የመከራው ተካፋይ ለመሆንና በሞቱም እርሱን ለመምሰል ነው። እንዲሁም ከሞትኩ በኋላ ተነሥቼ ለዘለዓለም በሕይወት ለመኖር ተስፋ በማድረግ ነው። ይህን ሁሉ ገና አላገኘሁም፤ ወይም በዚህ ሁሉ ፍጹም ሆኜአለሁ ለማለት አልችልም፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔን የእርሱ አድርጎ ያዘጋጀልኝን ሽልማት ለማግኘት ወደፊት በመሮጥ እተጋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ! ገና ወደዚያ እንደ ደረስኩ አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ይኸውም በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው። እንግዲህ በመንፈሳዊ ሕይወት የጠነከርን ሁሉ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፤ የምትለያዩበት ሐሳብ በመካከላችሁ ቢኖር ይህንንም ሐሳብ እግዚአብሔር ግልጥ ያደርግላችኋል። ያም ሆነ ይህ እስከ አሁን ከደረስንበት መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! የእኔን ምሳሌነት ለመከተል ተባበሩ፤ የእኛንም ምሳሌነት የሚከተሉትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ከአሁን በፊት ብዙ ጊዜ እንደ ነገርኳችሁና አሁንም እንባዬን እያፈሰስኩ እንደምነግራችሁ ሁሉ ብዙዎቹ በአካሄዳቸው የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነዋል። የእነርሱ አምላክ ሆዳቸው ነው፤ አሳፋሪ የሆነ ነገር ለእነርሱ ክብራቸው ነው፤ ሐሳባቸውም የሚያተኲረው በምድራዊ ነገር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእነርሱ መጨረሻ ጥፋት ነው። እኛ ግን የሰማይ መንግሥት ዜጎች ነን፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን። እርሱ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ የእርሱን ክቡር ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል፤ ይህንንም የሚያደርገው ሁሉን በሥልጣኑ ሥር ለማድረግ በሚያስችለው ኀይል ነው።
ፊልጵስዩስ 3:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ። ለእናንተ ተመሳሳይ የሆነን ነገር መልሼ ለመጻፍ ለእኔ አይታክተኝም፤ ይህ ለእናንተ ለደኅንነት የሆነ ነውና። ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፤ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን በእውነትም ከተገረዙት ወገን የሆንን ነንና። እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት ነገር ያለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ጥቅም የሚያስገኘውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ ለማወቅ ስል ሁሉ ነገር ጉዳት እንደሆነ አድርጌ እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ነገሮች በማጣት ተጐዳሁ፤ እነርሱንም እንደ ጉድፍ አድርጌ ቈጠርኋቸው፤ በዚህም ክርስቶስን እንዳገኝ፥ በክርስቶስም በማመን በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንጂ በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴ ጽድቅ ሳይኖረኝ፥ በእርሱ እንድገኝ ነው፤ በሞቱም እርሱን በመምሰል ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል መከራውንም ተካፋይ መሆኔን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ምናልባትም ቢሆንልኝ የሙታን ትንሣኤን እቀዳጃለሁ። እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍጹም ለመሆን አልበቃሁም፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደ ፊት እሮጣለሁ። ወንድሞች ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደ ፊት እዘረጋለሁ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያለውን የመጠራት ሽልማት እንዳገኝ ወደ ግቡ እሮጣለሁ። እንግዲህ በአእምሮ የበሰልን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም ለእናንተ ምሳሌ እንደ ሆንን እንዲሁ የሚመላለሱትን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ ነገርኋችሁ፤ አሁንም እያነባሁ ስለ እነርሱ እነግራችኋለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ደግሞ ለራሱ ሁሉን ነገር በሥሩ ለማስገዛት በሚችልበት ኃይሉ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።