ፊልጵስዩስ 2:8-11
ፊልጵስዩስ 2:8-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፥ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ።