ፊልጵስዩስ 2:2-11 - Compare All Versions
ፊልጵስዩስ 2:2-11 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ። ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ። ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደ አደረገልን ይህን አስቡ። ይኸውም የእግዚአብሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም። ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ፥ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:2-11 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:2-11 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቍኦጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ፊልጵስዩስ 2:2-11 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ስለዚህ በሐሳብ፥ በፍቅር፥ በመንፈስ፥ በዓላማ እየተስማማችሁ ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን አድርጉ። በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቊጠሩ እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በዚህ ዐይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ሥራ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል። እርሱ ሁልጊዜ የመለኮት ባሕርይ አለው። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባሕርይ በኃይል እንደ ያዘ አልቈጠረውም። ይልቁንም ያለውን ክብር ሁሉ ትቶ እንደ ባሪያ ሆኖ ታየ እንደ ሰውም ተወለደ፤ በሰው አምሳልም ተገለጠ፤ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፥ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ።
ፊልጵስዩስ 2:2-11 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው።