ፊልጵስዩስ 2:12-30

ፊልጵስዩስ 2:12-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አሁ​ንም ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ ዘወ​ትር እን​ደ​ም​ት​ሰ​ሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይ​ሆን፥ ሳል​ኖ​ርም በፍ​ር​ሀ​ትና በመ​ን​ቀ​ጥ​ቀጥ ሆና​ችሁ ለድ​ኅ​ነ​ታ​ችሁ ሥሩ። ለሚ​ወ​ደው ሥራ የሚ​ረ​ዳ​ችሁ እርሱ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይቅ​ር​ታ​ውን ይፈ​ጽ​ም​ላ​ችሁ። የም​ት​ሠ​ሩ​ትን ሁሉ ያለ ማን​ጐ​ራ​ጐ​ርና ያለ መጠ​ራ​ጠር በፍ​ቅ​ርና በስ​ም​ም​ነት ሥሩ። እንደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች ንጹ​ሓ​ንና የዋ​ሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማ​ያ​ም​ኑና በጠ​ማ​ሞች ልጆች መካ​ከል ነውር ሳይ​ኖ​ር​ባ​ችሁ በዓ​ለም እንደ ብር​ሃን ትታ​ያ​ላ​ችሁ፤ የሕ​ይ​ወ​ትን ቃል እያ​ስ​ተ​ማ​ራ​ችሁ፤ ክር​ስ​ቶስ በሚ​መ​ጣ​በት ቀን እኔ እን​ድ​መካ፤ የሮ​ጥሁ በከ​ንቱ አይ​ደ​ለ​ምና፤ የደ​ከ​ም​ሁም በከ​ንቱ አይ​ደ​ለ​ምና። ስለ ሃይ​ማ​ኖ​ታ​ች​ሁም የአ​ም​ልኮ መሥ​ዋ​ዕ​ትን እሠ​ዋ​ለሁ። እነ​ሆም እኔ በእ​ና​ንተ ደስ ይለ​ኛል፤ እና​ን​ተም በእኔ ደስ ይበ​ላ​ችሁ። ከእ​ኔም ጋር ሐሤት አድ​ርጉ። ጢሞ​ቴ​ዎ​ስን እን​ድ​ል​ክ​ላ​ችሁ፥ እኔም ዜና​ች​ሁን ሰምቼ ደስ እን​ዲ​ለኝ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ተስፋ አደ​ር​ጋ​ለሁ። ከእ​ርሱ በቀር፥ እንደ እኔ ሆኖ በማ​ስ​ተ​ዋል ግዳ​ጃ​ች​ሁን የሚ​ፈ​ጽም የለ​ኝ​ምና። የክ​ር​ስ​ቶ​ስን ያይ​ደለ፥ ሁሉም የራ​ሱን ጉዳይ ያስ​ባ​ልና። ልጅ አባ​ቱን እን​ደ​ሚ​ያ​ገ​ለ​ግል፥ በወ​ን​ጌል ትም​ህ​ርት እንደ አገ​ለ​ገ​ለኝ፥ የዚ​ህን ሰው ጠባ​ዩን ታው​ቃ​ላ​ችሁ። እን​ግ​ዲህ እን​ዴት እንደ አለሁ በዐ​ወ​ቅሁ ጊዜ፥ እር​ሱን በቶሎ እን​ደ​ም​ል​ከው ተስፋ አደ​ር​ጋ​ለሁ፤ እኔም ፈጥኜ እን​ደ​ም​መጣ በጌ​ታ​ችን አም​ና​ለሁ። አሁ​ንም አብ​ሮኝ የሚ​ሠ​ራ​ውን ወን​ድ​ማ​ች​ንን አፍ​ሮ​ዲ​ጡን ወደ እና​ንተ ልል​ከው አስ​ቤ​አ​ለሁ፤ እር​ሱም የክ​ር​ስ​ቶስ ሎሌ ነው፤ ለእ​ና​ን​ተም መም​ህ​ራ​ችሁ ነው፤ ለእ​ኔም ለች​ግሬ ጊዜ መል​እ​ክ​ተ​ኛዬ ነው። እንደ ታመመ፥ ለሞ​ትም እንደ ደረሰ መስ​ማ​ታ​ች​ሁን ዐውቆ ሊያ​ያ​ችሁ ይሻ​ልና። ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ማረው፤ በኀ​ዘን ላይ ኀዘን እን​ዳ​ይ​ጨ​መ​ር​ብኝ ለእ​ኔም እንጂ ለእሱ ብቻ አይ​ደ​ለም። እን​ድ​ታ​ዩ​ትና ደስ እን​ዲ​ላ​ችሁ፥ እኔም እን​ዳ​ላ​ዝን በቶሎ እል​ከ​ዋ​ለሁ። እን​ግ​ዲህ በጌ​ታ​ችን በፍ​ጹም ደስታ ተቀ​በ​ሉት፤ እን​ደ​ዚህ ያሉ​ት​ንም ሁሉ አክ​ብ​ሩ​አ​ቸው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ ስለ መሥ​ራት እስከ ሞት ደር​ሶ​አ​ልና፥ ከእኔ መል​እ​ክ​ትም እና​ንተ ያጐ​ደ​ላ​ች​ሁ​ትን ይፈ​ጽም ዘንድ ሰው​ነ​ቱን አሳ​ልፎ ሰጥ​ቶ​አ​ልና።

ፊልጵስዩስ 2:12-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋራ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋራ ደስ ልትሠኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል። ስለ እናንተ ሰምቼ ደስ እንዲለኝ፣ ጢሞቴዎስን ቶሎ ወደ እናንተ ልልክላችሁ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገድደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤ ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉና። ነገር ግን እንደምታውቁት ጢሞቴዎስ ማንነቱን አስመስክሯል፤ ልጅ ከአባቱ ጋራ እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋራ በወንጌል ሥራ አገልግሏልና። እንግዲህ የራሴን የወደ ፊት ሁኔታ እንዳጣራሁ ልልከው ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም ራሴ ቶሎ እንደምመጣ በጌታ ታምኛለሁ። እንዲሁም ወንድሜን፣ ዐብሮ ሠራተኛዬና ዐብሮኝ ወታደር የሆነውን፣ በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲንከባከበኝ የላካችሁትን፣ የእናንተ መልእክተኛ የሆነውና አገልጋዩን አፍሮዲጡን መልሼ እንድልክላችሁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እርሱ ሁላችሁንም ይናፍቃልና፤ መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቋል። በርግጥም ታምሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ምሕረት አደረገለት፤ በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር እንጂ ለርሱ ብቻ አይደለም። ስለዚህ እርሱን እንደ ገና ስታዩ ደስ እንዲላችሁና የእኔም ጭንቀት እንዲቀልል ልልከው በጣም ጓጕቻለሁ። በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች አክብሯቸው። እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሣሣ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና።

ፊልጵስዩስ 2:12-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ። ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ ሁላችሁን ይናፍቃልና፥ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። እንግዲህ እንደ ገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በብዙ ፍጥነት እልከዋለሁ። እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፥ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ፊልጵስዩስ 2:12-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል። ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው። ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ። እኔ ስለ እናንተ ሁኔታ በመስማት እንድጽናና ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ ለመላክ እንደሚያስችለኝ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። ስለ እናንተ ሁኔታ ከልብ የሚያስብ ከጢሞቴዎስ በቀር ሌላ ሰው የለኝም። ሌሎቹ ግን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ያሳድዳሉ እንጂ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ግድ የላቸውም። ጢሞቴዎስ፥ ታማኝነቱ ተፈትኖ የተመሰከረለት መሆኑንና ከእኔም ጋር እንደ አባትና ልጅ ተባብረን ወንጌልን በማስተማር አብረን ስንሠራ መቈየታችንን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ የእኔ ጉዳይ ከምን እንደሚደርስ ከተረዳሁ በኋላ ጢሞቴዎስን በፍጥነት ወደ እናንተ እንደምልክላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። እንዲያውም እኔ ራሴ በቶሎ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ጌታ ይረዳኛል ብዬ እተማመናለሁ። እንዲሁም እኔን በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲረዳኝ ልካችሁት የነበረውን ወንድሜን ኤጳፍሮዲቱስን ወደ እናንተ መላክ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ እርሱ ከእኔ ጋር የተሰለፈ ወታደርና የሥራ ጓደኛዬ ሆኖ ሲሠራ የቈየ ነው። እርሱን ወደ እናንተ የምልከውም ሁላችሁንም ለማየት በመናፈቁና እናንተም መታመሙን በመስማታችሁ ስለ ተጨነቀ ነው። በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምሕረት አደረገለት፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ሐዘን በሐዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር ምሕረት አደረገ። ስለዚህ እናንተ እርሱን በማየት እንድትደሰቱና የእኔም ሐዘን እንዲቃለል እርሱን ወደ እናንተ ልልከው በይበልጥ ፈለግኹ። እንግዲህ በጌታ አማኝ እንደ መሆኑ በደስታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች ሁሉ አክብሩአቸው። እናንተ በቅርብ ተገኝታችሁ ልታደርጉልኝ ያልቻላችሁትን ርዳታ እርሱ ለማሟላት ብሎ ስለ ክርስቶስ ሥራ ለሕይወቱ ሳይሳሳ ለሞት ተቃርቦ ነበር።

ፊልጵስዩስ 2:12-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ፤ እናንተም የሕይወትን ቃል በጽኑ በመያዛችሁ ምክንያት በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር አብራችሁ ሐሤት አድርጉ። ነገር ግን ስለ እናንተ ባወቅሁ ጊዜ ደስ ተሰኝቼ እንድበረታታ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እኔ ሆኖ ስለ ደኅንነታችሁ በቅንነት የሚጨነቅ እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝምና፤ የተቀሩት ሁሉ ግን የክርስቶስ ኢየሱስን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም የሚሹ ናቸውና። ነገር ግን ጢሞቴዎስ ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል በማገልገል መፈተኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ በእኔ ዘንድ ያለውን ሁኔታ አይቼ፥ እርሱን ቶሎ እንደምልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እኔም ራሴ ደግሞ ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛና ወታደር፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን ኤጳፍሮዲጡስን ወደ እናንተ መላክ ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ሁላችሁን ይናፍቃልና፤ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያደረገው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ደግሞ ነው። እንግዲህ እንደገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ ምክንያቱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለመፈጸም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ለክርስተቶስ ሥራ ሲል ለሞት ተቃርቦ ነበርና።

ፊልጵስዩስ 2:12-30

ፊልጵስዩስ 2:12-30 NASVፊልጵስዩስ 2:12-30 NASVፊልጵስዩስ 2:12-30 NASVፊልጵስዩስ 2:12-30 NASVፊልጵስዩስ 2:12-30 NASVፊልጵስዩስ 2:12-30 NASV