ፊልጵስዩስ 2:1-18 - Compare All Versions
ፊልጵስዩስ 2:1-18 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
አሁንም በክርስቶስ ደስታ፥ ወይም በፍቅር የልብ መጽናናት፥ ወይም የመንፈስ አንድነት፥ ወይም ማዘንና መራራትም በእናንተ ዘንድ ካለ፦ እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ። ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ። ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደ አደረገልን ይህን አስቡ። ይኸውም የእግዚአብሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም። ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ፥ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው። አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፥ ሳልኖርም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ። ለሚወደው ሥራ የሚረዳችሁ እርሱ እግዚአብሔር ይቅርታውን ይፈጽምላችሁ። የምትሠሩትን ሁሉ ያለ ማንጐራጐርና ያለ መጠራጠር በፍቅርና በስምምነት ሥሩ። እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ የሕይወትን ቃል እያስተማራችሁ፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን እኔ እንድመካ፤ የሮጥሁ በከንቱ አይደለምና፤ የደከምሁም በከንቱ አይደለምና። ስለ ሃይማኖታችሁም የአምልኮ መሥዋዕትን እሠዋለሁ። እነሆም እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ እናንተም በእኔ ደስ ይበላችሁ። ከእኔም ጋር ሐሤት አድርጉ።
ፊልጵስዩስ 2:1-18 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ከክርስቶስ ጋራ ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቍርባን ብፈስስ እንኳ ከሁላችሁ ጋራ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ። እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋራ ደስ ልትሠኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።
ፊልጵስዩስ 2:1-18 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቍኦጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።
ፊልጵስዩስ 2:1-18 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
በክርስቶስ መበረታታት ካላችሁ፥ በፍቅሩም የተጽናናችሁ ከሆነ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ኅብረት ካላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግነትንና ርኅራኄን ካሳያችሁ፥ ስለዚህ በሐሳብ፥ በፍቅር፥ በመንፈስ፥ በዓላማ እየተስማማችሁ ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን አድርጉ። በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቊጠሩ እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በዚህ ዐይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ሥራ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል። እርሱ ሁልጊዜ የመለኮት ባሕርይ አለው። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባሕርይ በኃይል እንደ ያዘ አልቈጠረውም። ይልቁንም ያለውን ክብር ሁሉ ትቶ እንደ ባሪያ ሆኖ ታየ እንደ ሰውም ተወለደ፤ በሰው አምሳልም ተገለጠ፤ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፥ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ። ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ። እግዚአብሔር ታዛዥነትን ለእናንተ እየሰጠ ዓላማውን ከፍጻሜ ለማድረስ በእናንተ ውስጥ ይሠራል። ማናቸውንም ሥራ በምትሠሩበት ጊዜ አታጒረምርሙ ወይም አትከራከሩ። ይህም ከሆነ በዚህ በጠማማና በመጥፎ ትውልድ መካከል ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ንጹሓን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት ታበራላችሁ። ይህም የሚሆነው ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ሳታቋርጡ አጥብቃችሁ በመያዝ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሩጫዬም ሆነ ሥራዬ ከንቱ ሆኖ ስለማይቀር ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የምመካበት ምክንያት ይኖረኛል ማለት ነው። ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ። እንዲሁም እናንተ ተደስታችሁ እኔንም የደስታችሁ ተካፋይ ታደርጉኛላችሁ።
ፊልጵስዩስ 2:1-18 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ስለዚህ ለእናንተ በክርስቶስ አንዳች መበረታተታት ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናትም ቢሆን፥ የመንፈስም ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄም ቢሆኑ፥ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ፤ እናንተም የሕይወትን ቃል በጽኑ በመያዛችሁ ምክንያት በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር አብራችሁ ሐሤት አድርጉ።