ፊልጵስዩስ 2:1-11

ፊልጵስዩስ 2:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አሁ​ንም በክ​ር​ስ​ቶስ ደስታ፥ ወይም በፍ​ቅር የልብ መጽ​ና​ናት፥ ወይም የመ​ን​ፈስ አን​ድ​ነት፥ ወይም ማዘ​ንና መራ​ራ​ትም በእ​ና​ንተ ዘንድ ካለ፦ እር​ሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክ​ርም ሆና​ችሁ፥ በፍ​ቅር ትኖሩ ዘንድ ደስ​ታ​ዬን ፈጽ​ሙ​ልኝ። በክ​ር​ክ​ርና ከንቱ ውዳ​ሴን በመ​ው​ደድ አት​ሥሩ፤ ትሕ​ት​ናን በያዘ ልቡና ከራ​ሳ​ችሁ ይልቅ ባል​ን​ጀ​ራ​ች​ሁን አክ​ብሩ እንጂ አት​ታ​በዩ። ለባ​ል​ን​ጀ​ራ​ች​ሁም እንጂ ለየ​ራ​ሳ​ችሁ ብቻ አታ​ስቡ። ፍጹ​ማን የሆ​ና​ችሁ ሁላ​ችሁ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ለእኛ እንደ አደ​ረ​ገ​ልን ይህን አስቡ። ይኸ​ውም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሆነ አይ​ደ​ለም። ነገር ግን የባ​ር​ያን መልክ ይዞ፥ በሰ​ውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደ​ረገ። እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋ​ረደ፤ ለሞት እስከ መድ​ረ​ስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመ​ስ​ቀል የሆ​ነው ነው። ስለ​ዚ​ህም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደ​ረ​ገው፤ ከስም ሁሉ የሚ​በ​ልጥ ስም​ንም ሰጠው። ይህም በሰ​ማ​ይና በም​ድር በቀ​ላ​ያ​ትና ከም​ድር በታች ያለ ጕል​በት ሁሉ ለኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ስም ይሰ​ግድ ዘንድ ነው። አን​ደ​በ​ትም ሁሉ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው።

ፊልጵስዩስ 2:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከክርስቶስ ጋራ ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

ፊልጵስዩስ 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቍኦጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

ፊልጵስዩስ 2:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በክርስቶስ መበረታታት ካላችሁ፥ በፍቅሩም የተጽናናችሁ ከሆነ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ኅብረት ካላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግነትንና ርኅራኄን ካሳያችሁ፥ ስለዚህ በሐሳብ፥ በፍቅር፥ በመንፈስ፥ በዓላማ እየተስማማችሁ ደስታዬ የተሟላ እንዲሆን አድርጉ። በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቊጠሩ እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በዚህ ዐይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የትሕትና ሥራ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል። እርሱ ሁልጊዜ የመለኮት ባሕርይ አለው። ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባሕርይ በኃይል እንደ ያዘ አልቈጠረውም። ይልቁንም ያለውን ክብር ሁሉ ትቶ እንደ ባሪያ ሆኖ ታየ እንደ ሰውም ተወለደ፤ በሰው አምሳልም ተገለጠ፤ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ፥ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ወዳለው የክብር ስፍራ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጠውንም ስም ሰጠው። ስለዚህ ለኢየሱስ ስም ክብር፥ በሰማይና በምድር፥ ከምድር በታችም ያሉት ሁሉ በጒልበታቸው ይንበረከካሉ። በአንደበታቸውም “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው በመመስከር ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሰጣሉ።

ፊልጵስዩስ 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ለእናንተ በክርስቶስ አንዳች መበረታተታት ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናትም ቢሆን፥ የመንፈስም ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄም ቢሆኑ፥ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው።