ፊልጵስዩስ 1:27-30
ፊልጵስዩስ 1:27-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ምናልባት የመጣሁ እንደ ሆነ፥ ሳልኖርም ቢሆን በወንጌል ሃይማኖት እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስና በአንድ አካል ጸንታችሁ እንደምትኖሩ አይና እሰማ ዘንድ ሥራችሁ ለክርስቶስ ትምህርት እንደሚገባ ይሁን። የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ። ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም። እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ።
ፊልጵስዩስ 1:27-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ፤ ይህ ከሆነ መጥቼ ባያችሁ ወይም በርቀት ሆኜ ስለ እናንተ ብሰማ፣ ለወንጌል እምነት እንደ አንድ ሰው ሆናችሁ በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ እንደምትቆሙ ዐውቃለሁ። በማንኛውም መንገድ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ፤ ይህ እነርሱ እንደሚጠፉ፣ እናንተ ግን እንደምትድኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት ነው። በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቷችኋልና፤ ቀድሞ እንዳያችሁትና አሁንም በእኔ እንዳለ በምትሰሙት በዚያው ዐይነት ተጋድሎ እናንተም እያለፋችሁ ነውና።
ፊልጵስዩስ 1:27-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።
ፊልጵስዩስ 1:27-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ከሁሉም በላይ ሕይወታችሁ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስመሰግን ይሁን፤ ይህም እኔ መጥቼ ባያችሁም ወይም ከእናንተ ብርቅ በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ መቆማችሁንና ወንጌልን በኅብረት ለማዳረስ መጋደላችሁን እሰማለሁ። ተቃዋሚዎቻችሁንም በምንም ነገር አትፍሩአቸው፤ ይህም ድፍረታችሁ ለእነርሱ የመጥፋታቸው ምልክት ሲሆን ለእናንተ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ የመዳኛችሁ ምልክት ነው። ክርስቶስን የማገልገል ዕድል የተሰጣችሁ በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቀበሉም ጭምር ነው። ስለዚህ አሁን ከእኔ ጋር የመከራ ተካፋዮች ሆናችኋል፤ ይህም መከራ ከዚህ በፊት ደርሶብኝ ያያችሁትና አሁንም እየደረሰብኝ መሆኑን የምትሰሙት ነው።
ፊልጵስዩስ 1:27-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ብቻ ኑሩ፤ በዚህም መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል እምነት አብራችሁ መጋደላችሁንና በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን እሰማለሁ። በምንም ዓይነት ነገር በተቃዋሚዎቻችሁ አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለ ሆነም በክርስቶስ የምታምኑ ብቻ ሳትሆኑ ስለ እርሱ መከራንም ደግሞ የምትቀበሉ ትሆናላችሁ፤ ይህም ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንደሆነ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።