ፊልጵስዩስ 1:18-26

ፊልጵስዩስ 1:18-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ነገር ግን ምን አለ? በየ​ም​ክ​ን​ያቱ በእ​ው​ነ​ትም ቢሆን፥ በሐ​ሰ​ትም ቢሆን፥ ስለ ክር​ስ​ቶስ ይና​ገ​ራሉ፤ ሰው​ንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠ​ራሉ፤ በዚ​ህም ደስ ብሎ​ኛል፤ ወደ​ፊ​ትም ደስ ይለ​ኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸ​ሎ​ታ​ች​ሁና በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ መን​ፈስ ወደ ሕይ​ወት እን​ደ​ም​ታ​ደ​ር​ሰኝ አው​ቃ​ለሁ። በም​ንም እን​ደ​ማ​ላ​ፍር ተስፋ እንደ አደ​ረ​ግ​ሁና እን​ደ​ታ​መ​ንሁ እንደ ወት​ሮው በልብ ደስታ በግ​ል​ጥ​ነት፥ አሁ​ንም የክ​ር​ስ​ቶስ ክብር በሕ​ይ​ወ​ቴም ቢሆን፥ በሞ​ቴም ቢሆን በሰ​ው​ነቴ ይገ​ለ​ጣል። እኔ በሕ​ይ​ወት ብኖ​ርም ክር​ስ​ቶ​ስን ለማ​ገ​ል​ገል ነው፤ ብሞ​ትም ዋጋ አለኝ። ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆ​ንም ምን እን​ደ​ም​መ​ርጥ አላ​ው​ቅም። በእ​ነ​ዚህ በሁ​ለቱ እጨ​ነ​ቃ​ለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከ​ክ​ር​ስ​ቶ​ስም ዘንድ ልኖር እወ​ዳ​ለሁ፤ ይል​ቁ​ንም ለእኔ ይህ ይሻ​ለ​ኛል፤ ይበ​ል​ጥ​ብ​ኛ​ልም። ደግ​ሞም ስለ እና​ንተ በሕ​ይ​ወተ ሥጋ ብኖር ይሻ​ላል። ይህ​ንም ዐውቄ ለማ​ደ​ጋ​ች​ሁና በሃ​ይ​ማ​ኖ​ትም ለም​ታ​ገ​ኙት ደስታ እን​ደ​ም​ኖር አም​ና​ለሁ። ዳግ​መኛ ወደ እና​ንተ በመ​ም​ጣቴ በእኔ ምክ​ን​ያት በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ የም​ታ​ገ​ኙት ክብር ይበ​ዛ​ላ​ችሁ ዘንድ።

ፊልጵስዩስ 1:18-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በእውነትም ሆነ በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና። በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል። ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው። በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋራ ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ለእናንተ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ይህን በማስተዋል፣ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ፣ በሁላችሁ ዘንድ እንደምቈይና እንደምኖር ተረድቻለሁ። እንደ ገና መጥቼ በእናንተ ዘንድ በምሆንበት ጊዜ፣ በእኔ ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁ ደስታ ይበዛላችኋል።

ፊልጵስዩስ 1:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቍኦይ አውቃለሁ።

ፊልጵስዩስ 1:18-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው። በሌላ በኩል በሕይወት መኖሬ ለእናንተ የበለጠ አስፈላጊ ነው። በዚህ በመተማመን እኔ ከሞት ተርፌ እምነታችሁ እንዲያድግና ደስታን እንድታገኙ ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ ዐውቃለሁ። እኔም እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ በእኔ ምክንያት ያላችሁ ትምክሕት በኢየሱስ ክርስቶስ ይበዛል።

ፊልጵስዩስ 1:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖር ማለት ለእኔ ፍሬያማ ሥራ የምሠራበት ቢሆን፥ ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህም በሁለቱ አማራጮች መካከል እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን ስለ እናንተ በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነገር ነው። ይህንንም ተረድቼ፥ በእምነት እንድታድጉና ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ከሁላችሁም ጋር እንደምቈይና እንደምኖር አውቃለሁ፤ በዚህም በእናንተ ዘንድ እንደገና ስለ መገኘቴ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ መመካታችሁ በእኔ እንዲበዛላችሁ ነው።