ፊልጵስዩስ 1:18-21
ፊልጵስዩስ 1:18-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ። በምንም እንደማላፍር ተስፋ እንደ አደረግሁና እንደታመንሁ እንደ ወትሮው በልብ ደስታ በግልጥነት፥ አሁንም የክርስቶስ ክብር በሕይወቴም ቢሆን፥ በሞቴም ቢሆን በሰውነቴ ይገለጣል። እኔ በሕይወት ብኖርም ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ።
ፊልጵስዩስ 1:18-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በእውነትም ሆነ በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና። በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል። ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው።
ፊልጵስዩስ 1:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።
ፊልጵስዩስ 1:18-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው።
ፊልጵስዩስ 1:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።