ፊልጵስዩስ 1:16-19
ፊልጵስዩስ 1:16-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና። በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም። ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ።
ፊልጵስዩስ 1:16-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ ዐስበው፣ በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በእውነትም ሆነ በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና።
ፊልጵስዩስ 1:16-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
ፊልጵስዩስ 1:16-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው። ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው።
ፊልጵስዩስ 1:16-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤