ፊልጵስዩስ 1:15-23

ፊልጵስዩስ 1:15-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከእ​ነ​ርሱ አን​ዳ​ን​ዶች በቅ​ና​ታ​ቸ​ውና በክ​ር​ክ​ራ​ቸው፥ ሌሎ​ችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክር​ስ​ቶስ ሊሰ​ብ​ኩና ሊያ​ስ​ተ​ምሩ የወ​ደዱ አሉ። በፍ​ቅር የሚ​ያ​ስ​ተ​ም​ሩም አሉ፤ ወን​ጌ​ልን ለማ​ስ​ተ​ማር እንደ ተሾ​ምሁ ያው​ቃ​ሉና። በኵ​ራት ስለ ክር​ስ​ቶስ የሚ​ያ​ስ​ተ​ምሩ ግን፥ ይህን አድ​ር​ገው በእ​ስ​ራቴ ላይ መከራ ሊጨ​ም​ሩ​ብኝ መስ​ሎ​አ​ቸው ነው እንጂ በእ​ው​ነት አይ​ደ​ለም፤ በቅ​ን​ነ​ትም አይ​ደ​ለም። ነገር ግን ምን አለ? በየ​ም​ክ​ን​ያቱ በእ​ው​ነ​ትም ቢሆን፥ በሐ​ሰ​ትም ቢሆን፥ ስለ ክር​ስ​ቶስ ይና​ገ​ራሉ፤ ሰው​ንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠ​ራሉ፤ በዚ​ህም ደስ ብሎ​ኛል፤ ወደ​ፊ​ትም ደስ ይለ​ኛል። እኔም ይህቺ ሥራ በጸ​ሎ​ታ​ች​ሁና በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ መን​ፈስ ወደ ሕይ​ወት እን​ደ​ም​ታ​ደ​ር​ሰኝ አው​ቃ​ለሁ። በም​ንም እን​ደ​ማ​ላ​ፍር ተስፋ እንደ አደ​ረ​ግ​ሁና እን​ደ​ታ​መ​ንሁ እንደ ወት​ሮው በልብ ደስታ በግ​ል​ጥ​ነት፥ አሁ​ንም የክ​ር​ስ​ቶስ ክብር በሕ​ይ​ወ​ቴም ቢሆን፥ በሞ​ቴም ቢሆን በሰ​ው​ነቴ ይገ​ለ​ጣል። እኔ በሕ​ይ​ወት ብኖ​ርም ክር​ስ​ቶ​ስን ለማ​ገ​ል​ገል ነው፤ ብሞ​ትም ዋጋ አለኝ። ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆ​ንም ምን እን​ደ​ም​መ​ርጥ አላ​ው​ቅም። በእ​ነ​ዚህ በሁ​ለቱ እጨ​ነ​ቃ​ለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከ​ክ​ር​ስ​ቶ​ስም ዘንድ ልኖር እወ​ዳ​ለሁ፤ ይል​ቁ​ንም ለእኔ ይህ ይሻ​ለ​ኛል፤ ይበ​ል​ጥ​ብ​ኛ​ልም።

ፊልጵስዩስ 1:15-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ ዐስበው፣ በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በእውነትም ሆነ በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር፣ በጸሎታችሁ አማካይነትና ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በተሰጠ ረድኤት ለመዳኔ እንደሚሆን ዐውቃለሁና። በምንም ዐይነት መንገድ ዐፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል። ለእኔ፣ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው። በሥጋ ከቈየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋራ ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና።

ፊልጵስዩስ 1:15-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤

ፊልጵስዩስ 1:15-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው። እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው። ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው።

ፊልጵስዩስ 1:15-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እርዳታ አማካይነት ለመዳኔ እንደሚሆንልኝ አውቄያለሁና፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በምንም ዓይነት ነገር አላፍርም፤ ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ እንደ ወትሮው እንዲሁ አሁንም በሥጋዬ ይከብራል ብዬ በሙሉ ድፍረት እናገራለሁ። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖር ማለት ለእኔ ፍሬያማ ሥራ የምሠራበት ቢሆን፥ ምን እንደምመርጥ አላውቅም። በእነዚህም በሁለቱ አማራጮች መካከል እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤