ፊልጵስዩስ 1:15-18
ፊልጵስዩስ 1:15-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ። በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና። በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም። ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል።
ፊልጵስዩስ 1:15-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ ዐስበው፣ በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታዲያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በእውነትም ሆነ በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤
ፊልጵስዩስ 1:15-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
ፊልጵስዩስ 1:15-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው። እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው። ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል።
ፊልጵስዩስ 1:15-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤ እነዚህ የኋለኞቹ ወንጌልን ለመመከት እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፤ እነዚያ የፊተኞቹ ግን በእስራቴ ላይ መከራን የሚያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ያለ ንጹሕ ልቦና ከራስ ወዳድነት በመነሣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ዳሩ ግን ይህ አድራጎታቸው ግድ የሚል ምን ነገር አለው? ብቻ በማመካኘትም ሆነ በእውነት በሁሉ መንገድ ክርስቶስ ይሰበክ እንጂ፤ ስለ ሆነም እኔ በዚህ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤