ፊልጵስዩስ 1:12-15
ፊልጵስዩስ 1:12-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ስለ ክርስቶስ ስም መታሰሬም በአደባባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአል። ከወንድሞቻችንም ብዙዎቹ በእስራቴ ምክንያት በጌታ ታመኑ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት ጨክነው ያስተምሩ ዘንድ እጅግ ተደፋፈሩ። ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ።
ፊልጵስዩስ 1:12-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁንም ወንድሞች ሆይ፣ በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ መርዳቱን ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። ከዚህ የተነሣ እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቋል። በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል። አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ።
ፊልጵስዩስ 1:12-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
ፊልጵስዩስ 1:12-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንድታውቁ እወዳለሁ። እኔም የታሰርኩት በክርስቶስ ምክንያት መሆኑን የቤተ መንግሥት ዘበኞችና ሌሎችም እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ። በእኔ መታሰር ምክንያት ከአማኞች ወንድሞች ብዙዎቹ በይበልጥ በጌታ የሚተማመኑ ሆነዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት ለማብሠር ከቀድሞ የበለጠ ድፍረት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው።
ፊልጵስዩስ 1:12-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ። ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ በክብር ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፤ በጌታ ካሉት ወንድሞች የሚበዙት በእስራቴ ላይ ጽኑ መተማመን ኖሩዋቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ደፍረዋል። በእርግጥ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ፤