ፊልሞና 1:8-21
ፊልሞና 1:8-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤ እኔ ጳውሎስ “እኔ እመልሰዋለሁ፤” ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም። አዎን፥ ወንድሜ ሆይ! በጌታ እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ።
ፊልሞና 1:8-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ማድረግ የሚገባህን እንድታደርግ አዝዝህ ዘንድ በክርስቶስ ድፍረት ቢኖረኝም፣ በፍቅር እለምንሃለሁ፤ እንግዲህ ሽማግሌና አሁን ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንሁት እኔ ጳውሎስ፣ በእስር እያለሁ ስለ ወለድሁት ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። አስቀድሞ የሚጠቅምህ አልነበረም፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ የሚጠቅም ሰው ሆኗል። የልቤ የሆነውን እርሱን መልሼ ወደ አንተ ልኬዋለሁ። ስለ ወንጌል በታሰርሁበት ጊዜ በአንተ ፈንታ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው ፈልጌ ነበር። ነገር ግን አንተ የምታደርገውን መልካም ነገር ሁሉ በውዴታ እንጂ በግዴታ እንዳይሆን ሳላማክርህ ምንም ማድረግ አልፈልግም። ምናልባት ለጥቂት ጊዜ ከአንተ የተለየው፣ ተቀብለህ ለዘለቄታው አንተ ዘንድ እንድታቈየው ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ በላይ የሆነ ተወዳጅ ወንድም ነው። ለእኔ ተወዳጅ ነው፤ ለአንተ ግን በሥጋም በጌታም ይበልጥ ተወዳጅ ነው። እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ከቈጠርኸኝ እኔን እንደምትቀበለኝ አድርገህ ተቀበለው። አንተን የበደለህ ነገር ቢኖር ወይም የአንተ ብድር ቢኖርበት በእኔ ላይ ቍጠረው። እኔ ጳውሎስ ይህን በገዛ እጄ ጽፌልሃለሁ፤ ያለበትን እኔው እከፍልሃለሁ። አንተም ራስህ የእኔ ስለ መሆንህ ምንም አልናገርም። ወንድሜ ሆይ፤ በጌታ እንድትጠቅመኝ እፈልጋለሁ፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። ታዛዥ መሆንህን በመተማመን፣ ከምጠይቀውም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ እጽፍልሃለሁ።
ፊልሞና 1:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም። እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቍኦጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤ እኔ ጳውሎስ፦ እኔ እመልሰዋለሁ ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም። አዎን፥ ወንድሜ ሆይ፥ በጌታ እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ።
ፊልሞና 1:8-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ተግባርህን ፈጽም ብዬ አንተን ለማዘዝ በክርስቶስ ድፍረት ነበረኝ፤ ሆኖም እንደዚያ ከማድረግ ይልቅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት እኔ ሽማግሌው ጳውሎስ በፍቅር መለመንን እመርጣለሁ። እኔ እስር ቤት እያለሁ ልጄ ስለ ሆነው ስለ ኦኔሲሞስ አንተን እለምንሃለሁ። አናሲሞስ ከዚህ በፊት አይጠቅምህም ነበር፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ ጠቃሚ ነው። እነሆ እርሱን ወደ አንተ መልሼ ልኬዋለሁ፤ እርሱን ወደ አንተ ስልከውም የገዛ ራሴን ልብ እንደ ላክሁ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። በወንጌል ምክንያት እዚህ ታስሬ ሳለሁ በአንተ ምትክ ሆኖ እንዲያገለግለኝ እርሱ ከእኔ ጋር ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር፤ ነገር ግን የአንተ መልካም ሥራ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ እንዲሆን ብዬ አንተን ሳላስፈቅድ ምንም ማድረግ አልፈለግሁም። ኦኔሲሞስ እስከ አሁን ለጥቂት ጊዜ የተለየህ ምናልባት ከእንግዲህ ወዲህ ለሁልጊዜ ከአንተ ጋር እንዲኖር ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ ጋር የሚኖረውም እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ የበለጠ ሆኖ እንደ ውድ ወንድም ነው፤ እርሱ ለእኔ ውድ ወንድም ነው፤ ይሁን እንጂ በሥጋ እርሱ በአገልግሎቱ ስለሚጠቅምህ በመንፈሱ ደግሞ በክርስቶስ ወንድምህ ስለ ሆነ ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ ነው። እንግዲህ እኔን እንደ ወንድም አድርገህ ከቈጠርከኝ ልክ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። ያደረሰብህ በደል ቢኖር ወይም ዕዳ ቢኖርበት ዕዳውን በእኔ ላይ አድርገው። እነሆ እኔ ጳውሎስ “ዕዳውን እከፍልሃለሁ” ብዬ በገዛ እጄ ጽፌ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሆኖም ስለ ሕይወትህ አንተ ራስህ እንኳ የእኔ ባለዕዳ መሆንክን እኔ ላስታውስህ አያስፈልግም። እንግዲህ ወንድሜ ሆይ! ይህን መልካም ነገር እንድታደርግልኝ በጌታ እለምንሃለሁ፤ እባክህ ልቤን በክርስቶስ አድስልኝ። ይህን የጻፍኩልህ እንደምትታዘዘኝ በመተማመን ነው፤ እንዲያውም እኔ ከምጠይቅህ በላይ እንደምታደርግ ዐውቃለሁ።
ፊልሞና 1:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ ኦኔሲሞስ እለምንሃለሁ፤ በፊት አልጠቀመህም ነበር፤ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም በጣም እየጠቀመን ነው። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበለው። እኔስ ስለ ወንጌል በገጠመኝ እስራት አንተን ወክሎ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው በፈቅድኩ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም ነገር ላደርግ አልፈልግሁም። ዳግመኛ ተቀብለህ ለዘለዓለም እንድትይዘው ይሆናል ምናልባት ለጊዜው የተለየህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባርያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም ሆነ በጌታ ዘንድ ከባርያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? እንግዲህ እንደ ወንድምህ እስከ ቆጠርከኝ ድረስ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር በድሎህ እንደሆነ ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር፤ እኔ ጳውሎስ “እኔ እመልሰዋለሁ፤” ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አላስታውስህም። አዎን፥ ወንድሜ ሆይ! በጌታ ይህንን ጉዳይ ፈጽምልኝ። በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። ከምጠይቅህ ይልቅ አብልጠህ እንደምታደርግ በማወቅ እንደምትታዘዝም በመተማመን እጽፍልሃለሁ።