ፊልሞና 1:4-16

ፊልሞና 1:4-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም?

ፊልሞና 1:4-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንተን በጸሎቴ በማስብህ ጊዜ አምላኬን ሁልጊዜ አመሰግናለሁ፤ ምክንያቱም በጌታ በኢየሱስ ያለህን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያለህን ፍቅር ሰምቻለሁ። በክርስቶስ ስላለን መልካም ነገር ሁሉ በሚገባ ትረዳ ዘንድ፣ እምነትህን ለሌሎች በማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ። ወንድሜ ሆይ፤ የቅዱሳንን ልብ ስላሳረፍህ ከፍቅርህ ታላቅ ደስታና መጽናናት አግኝቻለሁ። ስለዚህ ማድረግ የሚገባህን እንድታደርግ አዝዝህ ዘንድ በክርስቶስ ድፍረት ቢኖረኝም፣ በፍቅር እለምንሃለሁ፤ እንግዲህ ሽማግሌና አሁን ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንሁት እኔ ጳውሎስ፣ በእስር እያለሁ ስለ ወለድሁት ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። አስቀድሞ የሚጠቅምህ አልነበረም፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ የሚጠቅም ሰው ሆኗል። የልቤ የሆነውን እርሱን መልሼ ወደ አንተ ልኬዋለሁ። ስለ ወንጌል በታሰርሁበት ጊዜ በአንተ ፈንታ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው ፈልጌ ነበር። ነገር ግን አንተ የምታደርገውን መልካም ነገር ሁሉ በውዴታ እንጂ በግዴታ እንዳይሆን ሳላማክርህ ምንም ማድረግ አልፈልግም። ምናልባት ለጥቂት ጊዜ ከአንተ የተለየው፣ ተቀብለህ ለዘለቄታው አንተ ዘንድ እንድታቈየው ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ በላይ የሆነ ተወዳጅ ወንድም ነው። ለእኔ ተወዳጅ ነው፤ ለአንተ ግን በሥጋም በጌታም ይበልጥ ተወዳጅ ነው።

ፊልሞና 1:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም።

ፊልሞና 1:4-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በጸሎቴ አንተን እያሰብኩ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ በጌታ በኢየሱስ ያለህን እምነትና ለምእመናንም ያለህን ፍቅር ሰምቼአለሁ፤ የክርስቶስ በመሆናችን ያለን መልካም ነገር ሁሉ በይፋ ይታወቅ ዘንድ እምነትህን ለሌሎች ለማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ። ወንድሜ ሆይ! በአንተ ምክንያት የምእመናን ልብ ስለ ታደሰ ፍቅርህ ታላቅ ደስታንና መጽናናትን ሰጥቶኛል። ስለዚህ ተግባርህን ፈጽም ብዬ አንተን ለማዘዝ በክርስቶስ ድፍረት ነበረኝ፤ ሆኖም እንደዚያ ከማድረግ ይልቅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት እኔ ሽማግሌው ጳውሎስ በፍቅር መለመንን እመርጣለሁ። እኔ እስር ቤት እያለሁ ልጄ ስለ ሆነው ስለ ኦኔሲሞስ አንተን እለምንሃለሁ። አናሲሞስ ከዚህ በፊት አይጠቅምህም ነበር፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ ጠቃሚ ነው። እነሆ እርሱን ወደ አንተ መልሼ ልኬዋለሁ፤ እርሱን ወደ አንተ ስልከውም የገዛ ራሴን ልብ እንደ ላክሁ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። በወንጌል ምክንያት እዚህ ታስሬ ሳለሁ በአንተ ምትክ ሆኖ እንዲያገለግለኝ እርሱ ከእኔ ጋር ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር፤ ነገር ግን የአንተ መልካም ሥራ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ እንዲሆን ብዬ አንተን ሳላስፈቅድ ምንም ማድረግ አልፈለግሁም። ኦኔሲሞስ እስከ አሁን ለጥቂት ጊዜ የተለየህ ምናልባት ከእንግዲህ ወዲህ ለሁልጊዜ ከአንተ ጋር እንዲኖር ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ ጋር የሚኖረውም እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ የበለጠ ሆኖ እንደ ውድ ወንድም ነው፤ እርሱ ለእኔ ውድ ወንድም ነው፤ ይሁን እንጂ በሥጋ እርሱ በአገልግሎቱ ስለሚጠቅምህ በመንፈሱ ደግሞ በክርስቶስ ወንድምህ ስለ ሆነ ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ ነው።

ፊልሞና 1:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በጸሎቴ እያሰብኩህ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ። በጌታ በኢየሱስ ዘንድ፤ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለው ፍቅርህና እምነትህ እሰማለሁና። የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ ኦኔሲሞስ እለምንሃለሁ፤ በፊት አልጠቀመህም ነበር፤ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም በጣም እየጠቀመን ነው። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበለው። እኔስ ስለ ወንጌል በገጠመኝ እስራት አንተን ወክሎ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው በፈቅድኩ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም ነገር ላደርግ አልፈልግሁም። ዳግመኛ ተቀብለህ ለዘለዓለም እንድትይዘው ይሆናል ምናልባት ለጊዜው የተለየህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባርያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም ሆነ በጌታ ዘንድ ከባርያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም?