አብድዩ 1:1-21

አብድዩ 1:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የአ​ብ​ድዩ ራእይ። ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ ኤዶ​ም​ያስ እን​ዲህ ይላል፦ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ መስ​ማ​ትን ሰማሁ፤ ከባ​ቢን ወደ አሕ​ዛብ ልኮ፥ “ተነሡ፤ በላ​ይ​ዋም እን​ነ​ሣና እን​ው​ጋት። እነሆ በአ​ሕ​ዛብ ዘንድ ታናሽ አድ​ር​ጌ​ሃ​ለሁ፤ አንተ እጅግ ተን​ቀ​ሃል። በተ​ሰ​ነ​ጠ​ቀም ዓለት ውስጥ እን​ደ​ሚ​ኖር- ማደ​ሪ​ያ​ው​ንም ከፍ ከፍ እን​ደ​ሚ​ያ​ደ​ርግ፥ በል​ቡም፦ ወደ ምድር የሚ​ያ​ወ​ር​ደኝ ማን ነው? እን​ደ​ሚል፥ የል​ብህ ትዕ​ቢት እጅግ አኵ​ር​ቶ​ሃል። እንደ ንስር መጥ​ቀህ ብት​ወጣ፥ ቤት​ህም በከ​ዋ​ክ​ብት መካ​ከል ቢሆን፥ ከዚያ አወ​ር​ድ​ሃ​ለሁ፥” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። “ሌቦች ቢመ​ጡ​ብህ፥ ወይም ወን​በ​ዴ​ዎች በሌ​ሊት ቢመጡ፥ የሚ​በ​ቃ​ቸ​ውን የሚ​ሰ​ርቁ አይ​ደ​ሉ​ምን? ወይ​ንም የሚ​ቈ​ርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃር​ሚያ አያ​ስ​ቀ​ሩ​ምን? ዔሳ​ውን እን​ዴት መረ​መ​ሩት! የሸ​ሸ​ገ​ው​ንም እን​ዴት ወሰ​ዱ​በት! የተ​ማ​ማ​ል​ሃ​ቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳር​ቻህ ሰደ​ዱህ፤ የተ​ስ​ማ​ሙ​ህም ሰዎች ተነ​ሡ​ብህ፤ አሸ​ነ​ፉ​ህም፤ በበ​ታ​ች​ህም አሽ​ክላ ዘረ​ጉ​ብህ፤ እነ​ር​ሱም ማስ​ተ​ዋል የላ​ቸ​ውም። በዚያ ቀን ከኤ​ዶ​ም​ያስ ጥበ​በ​ኞ​ችን፥ ከዔ​ሳው ተራ​ራም ማስ​ተ​ዋ​ልን አጠ​ፋ​ለሁ ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ከዔ​ሳው ተራራ ሰዎች ሁሉ ይጠፉ ዘንድ የቴ​ማን ሰል​ፈ​ኞ​ችህ ይደ​ነ​ግ​ጣሉ። “በወ​ን​ድ​ምህ በያ​ዕ​ቆብ ላይ ስለ ተደ​ረገ ኀጢ​አ​ትና ግድያ ኀፍ​ረት ይከ​ድ​ን​ሃል፤ ለዘ​ለ​ዓ​ለ​ምም ትጠ​ፋ​ለህ። በፊቱ አን​ጻር በቆ​ምህ ቀን፥ አሕ​ዛብ ጭፍ​ራ​ውን በማ​ረ​ኩ​በት፥ እን​ግ​ዶ​ችም በበሩ በገ​ቡ​በት፥ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ዕጣ በተ​ጣ​ጣ​ሉ​በት ቀን አንተ ደግሞ ከእ​ነ​ርሱ እንደ አንዱ ነበ​ርህ። በጠ​ላት ቀን ወን​ድ​ም​ህን ዝቅ አድ​ር​ገህ ትመ​ለ​ከ​ተው ዘንድ፥ በጥ​ፋ​ታ​ቸ​ውም ቀን በይ​ሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭ​ን​ቀ​ታ​ቸ​ውም ቀን በት​ዕ​ቢት ትና​ገር ዘንድ ባል​ተ​ገ​ባህ ነበር። በች​ግ​ራ​ቸ​ውም ቀን በሕ​ዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥ​ፋ​ታ​ቸ​ውም ቀን ጉባ​ኤ​ያ​ቸ​ውን ትመ​ለ​ከት ዘንድ፥ በእ​ል​ቂ​ታ​ቸ​ውም ቀን በሠ​ራ​ዊ​ታ​ቸው ላይ አደጋ ትጥል ዘንድ አይ​ገ​ባ​ህም ነበር። የሸ​ሹ​ት​ንም ለማ​ጥ​ፋት በመ​ተ​ላ​ለ​ፊያ መን​ገ​ዳ​ቸው ትቆም ዘንድ፥ ድል በተ​ነ​ሡ​በ​ትም ቀን ከእ​ርሱ ያመ​ለ​ጡ​ትን ለማ​ስ​ጨ​ነቅ ትከ​ብ​ባ​ቸው ዘንድ ባል​ተ​ገ​ባህ ነበር። “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቀን በአ​ሕ​ዛብ ሁሉ ላይ ቀር​ቦ​አ​ልና፥ አንተ እንደ አደ​ረ​ግ​ኸው እን​ዲሁ ይደ​ረ​ግ​ብ​ሃል፤ ፍዳ​ህም በራ​ስህ ላይ ይመ​ለ​ሳል። በቅ​ዱሱ ተራ​ራዬ ላይ እንደ ጠጣህ እን​ዲሁ አሕ​ዛብ ሁሉ ወይ​ንን ይጠ​ጣሉ፤ አዎን፥ ይጠ​ጣሉ፥ ይጨ​ል​ጡ​ማል፤ እን​ዳ​ል​ነ​በ​ሩም ይሆ​ናሉ። “ነገር ግን በጽ​ዮን ተራራ ላይ መድ​ኀ​ኒት ይሆ​ናል፤ እር​ሱም ቅዱስ ይሆ​ናል፤ የያ​ዕ​ቆ​ብም ቤት ሰዎች የወ​ረ​ሱ​አ​ቸ​ውን ይወ​ር​ሳሉ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ተና​ግ​ሮ​አ​ልና የያ​ዕ​ቆብ ቤት እሳት፥ የዮ​ሴ​ፍም ቤት ነበ​ል​ባል፥ የዔ​ሳ​ውም ቤት ገለባ ይሆ​ናሉ፤ እነ​ር​ሱ​ንም ያቃ​ጥ​ሉ​አ​ቸ​ዋል፤ ይበ​ሉ​አ​ቸ​ው​ማል፤ ከዔ​ሳ​ውም ቤት ቅሬታ አይ​ኖ​ርም። የደ​ቡ​ብም ሰዎች የዔ​ሳ​ውን ተራራ፥ የቆ​ላ​ውም ሰዎች ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን ይወ​ር​ሳሉ፤ የኤ​ፍ​ሬ​ም​ንም ተራራ፥ የሰ​ማ​ር​ያን፥ የብ​ን​ያ​ም​ንና የገ​ለ​ዓ​ድን ሀገር ይወ​ር​ሳሉ። ይህም የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች የጭ​ፍ​ራ​ቸው ምርኮ የከ​ነ​ዓ​ንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራ​ጵታ ድረስ ይወ​ር​ሳል፤ የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ምር​ኮ​ኞች እስከ ኤፍ​ራታ ድረስ የደ​ቡ​ብን ከተ​ሞች ይወ​ር​ሳሉ። የዳ​ኑ​ትም የዔ​ሳ​ውን ተራራ ይበ​ቀ​ሉት ዘንድ ከጽ​ዮን ተራራ ይዘ​ም​ታሉ፤ መን​ግ​ሥ​ትም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይሆ​ናል።”

አብድዩ 1:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም እንዲህ ይላል፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምተናል፤ መልእክተኛው ወደ አሕዛብ ተልኮ እንዲህ ብሏል፤ “ተነሡ፤ እርሷን ለመውጋት እንውጣ።” “እነሆ፤ በአሕዛብ መካከል ታናሽ አደርግሃለሁ፤ እጅግ የተናቅህ ትሆናለህ። አንተ በሰንጣቃ ዐለት ውስጥ የምትኖር፣ መኖሪያህንም በከፍታ ስፍራ ያደረግህ፣ ለራስህም፣ ‘ማን ወደ ምድር ሊያወርደኝ ይችላል?’ የምትል፣ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ወደ ላይ ብትወጣ፣ ጐጆህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፣ ከዚያ ወደ ታች አወርድሃለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ሌቦች ወደ አንተ ቢመጡ፣ ዘራፊዎችም በሌሊት ቢገቡ፣ የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ያህል ብቻ አይደለምን? ወይን ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ፣ ጥቂት ቃርሚያ አይተዉምን? አንተ ግን ምንኛ ጥፋት ይጠብቅሃል! ዔሳው ግን እንዴት ተዘረፈ? የሸሸገውስ ሀብት ምንኛ ተመዘበረ! ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ድንበር ይገፉሃል፤ ጓደኞችህ ያታልሉሃል፤ ያሸንፉህማል፤ እንጀራህን የበሉ ወጥመድ ይዘረጉብሃል፤ አንተ ግን አታውቀውም። “በዚያ ቀን ጥበበኛ ሰዎችን ከኤዶም፣ አስተዋዮችንም ከዔሳው ተራሮች አልደመስስምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ቴማን ሆይ፤ ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ፤ በዔሳውም ተራሮች ያለ ሁሉ፣ ተገድሎ ይጠፋል። በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣ በዕፍረት ትሸፈናለህ፤ ለዘላለምም ትጠፋለህ። እንግዶች ሀብቱን ዘርፈው ሲሄዱ፣ ባዕዳንም በበሮቹ ሲገቡ፣ በኢየሩሳሌምም ላይ ዕጣ ሲጣጣሉ፣ በዚያ ቀን ገለልተኛ ሆነህ ተመለከትህ፣ አንተም ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆንህ። ክፉ ቀን በገጠመው ጊዜ፣ በወንድምህ ሥቃይ መደሰት አልነበረብህም፤ በጥፋታቸው ቀን፣ የይሁዳ ሕዝብ ሲያዝኑ ሐሤት ማድረግ አልነበረብህም፤ በጭንቀታቸውም ቀን፣ በትዕቢት ልትናገር አይገባህም ነበር። በጥፋታቸው ቀን፣ በሕዝቤ በር መግባት የለብህም ነበር፤ በጥፋታቸው ቀን፣ በጭንቀታቸው መደሰት አልነበረብህም፤ በጥፋታቸው ቀን፣ ሀብታቸውን መዝረፍ አይገባህም ነበር። ስደተኞቻቸውን ለመግደል፣ በመንታ መንገድ መጠባበቅ አይገባህም ነበር፤ በጭንቀታቸው ቀን፣ የተረፉትን አሳልፈህ መስጠት አልነበረብህም። “በአሕዛብ ሁሉ ላይ፣ የእግዚአብሔር ቀን ደርሷል፤ አንተ እንዳደረግኸው፣ በአንተም ላይ ይደረጋል፤ ክፉ ሥራህም በራስህ ላይ ይመለሳል። እናንተ በቅዱሱ ተራራዬ እንደ ጠጣችሁ፣ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤ ይጠጣሉ፤ አብዝተውም ይጠጣሉ፤ ከዚህም በፊት እንዳልሆኑት ይሆናሉ። ነገር ግን በጽዮን ተራራ ነጻ መውጣት ይሆናል፤ የያዕቆብ ቤትም እርሷ የተቀደሰች ትሆናለች፤ ርስታቸውን ይወርሳሉ። የያዕቆብ ቤት እሳት፣ የዮሴፍም ቤት ነበልባል ይሆናል፤ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናል፤ ያቃጥሉታል፤ ይበሉትማል፤ ከዔሳው ቤት የሚተርፍ አይኖርም።” እግዚአብሔር ተናግሯል። የኔጌብ ሰዎች፣ የዔሳውን ተራራ ይይዛሉ፤ ከተራራው ግርጌ ያሉ ሰዎችም፣ የፍልስጥኤማውያንን ምድር ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንና የሰማርያንም ዕርሻ ይይዛሉ፤ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። በከነዓን ያለው ይህ የእስራኤል ስደተኞች ወገን፣ እስከ ሰራፕታ ያለውን ምድር ይወርሳል፤ በሰፋራድም ያሉ የኢየሩሳሌም ስደተኞች፣ የኔጌብን ከተሞች ይወርሳሉ። የዔሳውን ተራሮች ለመግዛት፣ ነጻ አውጪዎች ወደ ጽዮን ተራራ ይወጣሉ፤ መንግሥቱም የእግዚአብሔር ይሆናል።

አብድዩ 1:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምተናል፥ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ፦ ተነሡ፥ በላይዋም በሰልፍ እንነሣ ብሎአል። እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፥ አንተ እጅግ ተንቀሃል። በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን? አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተመረመረ! የተሸሸገበት ነገር ምንኛ ተፈለገ! የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፥ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፥ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል እግዚአብሔር። ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በመገደል ይጠፉ ዘንድ ኃያላንህ ይደነግጣሉ። በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፥ ለዘላለምም ትጠፋለህ። በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ። ነገር ግን በመከራው ቀን ወንድምህን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ አይገባህም ነበር። በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ አይገባህም ነበር። የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ትቆም ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ትሰጥ ዘንድ አይገባህም ነበር። የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ። ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይሆናሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ የለውም። የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቈላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፥ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይሆናል።

አብድዩ 1:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አብድዩ ያየው ራእይ፦ እግዚአብሔር አምላክ ኤዶምን በተመለከተ አብድዩን ልኮአል፤ የሰማነውም የእግዚአብሔር መልእክት፦ “እኔ እግዚአብሔር በኤዶም ላይ አደጋ እንዲጥሉ በማዘዝ ወደ ሕዝቦች መልእክተኛ ልኬአለሁ!” የሚል ነው። እግዚአብሔር ኤዶምን እንዲህ ይላል፦ “እነሆ በአሕዛብ መካከል ደካማ አደርግሃለሁ፤ እጅግም የተናቅህ ትሆናለህ። የልብህ ትዕቢት አታሎሃል፤ በጠንካራ አለት በተመሸገ ከተማ ውስጥ ትኖራለህ፤ የምታድርበትም ቤት በከፍተኞች ተራራዎች ላይ የተሠራ ነው፤ ‘ካለሁበት ስፍራ ማን ሊያወርደኝ ይችላል?’ በማለት ትመካለህ። ነገር ግን እንደ ንስር ወደ ላይ ብትበር፥ መኖሪያህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ። ይህን እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።” “ሌቦች ወይም ቀማኞች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ያኽል ብቻ ይወስዳሉ፤ የወይን ምርትንም የሚሰበስቡ ቃርሚያ ይተዋሉ፤ የአንተ ጠላቶች ግን ፈጽሞ ያጠፉሃል። እናንተ የዔሳው ዘሮች ቤታችሁ ተበርብሯል፤ እነሆ ሀብታችሁ በሙሉ ተዘርፎአል። የቃል ኪዳን ጓደኞችህ ሁሉ አታለሉህ፤ ከሀገርህም አስወጥተው አሳደዱህ፤ ወዳጆችህ በአንተ ላይ በጠላትነት ተነሡብህ፤ ያንተን እንጀራ የበሉ ወጥመድ ዘረጉብህ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርጉብህ ግን አንተ አልደረስክበትም። “በዚያን ጊዜ ከኤዶም ጥበበኞችን፥ ከዔሳው ተራራ ዕውቀትን አጠፋለሁ። በኤዶም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይገደላሉ፤ የቴማንም ጀገኖች በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።” “የወንድምህን የያዕቆብን ዘሮች በግፍ ስለ ገደልክ፥ ትዋረዳለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። ጠላቶቻቸው በሮቻቸውን ሰባብረው፥ ሀብታቸውን ሁሉ በዘረፉበት ቀን፥ አንተ በዳር ቆመህ ትመለከት ነበር፤ አንተ እኮ ኢየሩሳሌምን በዕጣ ከተከፋፈሉአት ሰዎች በምንም አትሻልም። በይሁዳ አገር በሚኖሩ ወንድሞችህ ላይ በደረሰው መከራ፥ ልትደሰት ባልተገባህም ነበር፤ በጥፋታቸው ቀን ሐሤት ልታደርግና በጭንቀታቸውም ቀን በእነርሱ ላይ ልትታበይ ባልተገባህም ነበር። በችግራቸው ቀን ወደ ሕዝቤ በር ልትገባ ባልተገባህ ነበር፤ በመከራቸውም ቀን በይሁዳ ሕዝብ ጥፋት ለመደሰት መተባበር አይገባህም ነበር፤ በመጥፊያቸው ቀን የእነርሱን ንብረት መዝረፍ ባልተገባህም ነበር። የሚሸሹትን ለመግደል በመስቀልኛ መንገድ ላይ ባላደባህባቸውም ነበር፤ የተረፉትንም በመከራቸው ቀን ለጠላት አሳልፈህ መስጠት ባልተገባህም ነበር።” “እኔ እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ የምፈርድበት ቀን ደርሶአል፤ ኤዶም ሆይ! እንደ ሥራህ ዋጋህን ታገኛለህ፤ የምትፈጽመው ክፉ ሥራ በራስህ ላይ ይመለሳል። ሕዝቤ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ የመከራ ጽዋ ጠጥተዋል፤ በዙሪያው ያሉት አሕዛብ ሁሉ ከዚህ የከፋ የመከራ ጽዋ ይጠጣሉ፤ የጠጡትም ሁሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ።” “በጽዮን ተራራ ከጥፋት የሚያመልጡ ይገኛሉ፤ የጽዮን ተራራም የተቀደሰች ትሆናለች፤ የያዕቆብም ሕዝብ ተወስዶባቸው የነበረውን ንብረት መልሰው ይወስዳሉ። የያዕቆብ ልጆች እንደ እሳት፥ የዮሴፍ ልጆች እንደ ነበልባል፥ የዔሳውም ልጆች እንደ ገለባ ይሆናሉ፤ እሳት ገለባን እንደሚያቃጥል የያዕቆብና የዮሴፍ ልጆች የዔሳውን ልጆች ያጠፋሉ። ይህንንም የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ከይሁዳ በስተደቡብ ያሉ ሕዝቦች የኤዶምን ምድር ይወርሳሉ፤ በምዕራብ ተራራዎች ግርጌ በሚገኘው ቆላማ ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች የፍልስጥኤምን ምድር ይይዛሉ፤ የኤፍሬምንና የሰማርያንም ግዛት ይወስዳሉ፤ የብንያም ሰዎችም የገለዓድን ምድር ይወርሳሉ። በስደት ላይ የነበሩት የሰሜን እስራኤል ሕዝብ ሖላ ከሚባል አገር ተመልሰው የከነዓንን ምድር እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳሉ፤ በሰፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ስደተኞች በስተ ደቡብ ያሉትን ከተሞች ይይዛሉ። የዳኑት የኢየሩሳሌም ሰዎች በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው ኤዶምን ይገዛሉ፤ መንግሥቱም የእግዚአብሔር ይሆናል።”

አብድዩ 1:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የአብድዩ ራእይ። ጌታ አምላክ ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከጌታ መልእክት ሰምተናል፥ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ፦ ተነሡ፥ በላይዋም በጦርነት እንነሣ ብሏል። እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፥ አንተ እጅግ ተንቀሃል። በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ። ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ብቻ ይሰርቁ የለምን? ወይንንም የሚቆርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ ያስቀሩ የለምን? አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተበረበረ! ብርቅዬ ሀብቱ ምንኛ ተፈለገ! ከአንተ ጋር ቃል የተገባቡ ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፥ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፥ በበታችህም ወጥመድ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል ጌታ። ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በግድያ እንዲጠፉ ኃያላን ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ። በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገው ግፍ እፍረትን ትከናነባለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። በዳር ቆመህ በተመለከትክበት ቀን፥ አሕዛብ ሀብቱን በማረኩበት፥ ባእዳን በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተም እንደ እነርሱ ነበርህ። ነገር ግን በወንድምህ የመከራ ቀን ልትደሰት፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች መጥፋት ደስ ሊልህ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ልትናገር አይገባም ነበር። በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ልትገባ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ልትመለከት፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ልትዘረጋ አይገባህም ነበር። የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ልትቆም፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ልትሰጥ አይገባህም ነበር። የጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቧልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ። ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይኖራሉ፥ እርሱም የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። ጌታ ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት የሚተርፍ አይኖርም። የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። ይህም የእስራኤል ልጆች የጦር ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለጌታ ይሆናል።