ዘኍልቍ 25:1-18 - Compare All Versions
ዘኍልቍ 25:1-18 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እስራኤልም በሰጢን አደሩ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር አመነዘሩ፤ ረከሱም። ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም መሥዋዕታቸውን በሉ፤ ለአምላኮቻቸውም ሰገዱ። እስራኤልም ለብዔል ፌጎር ራሳቸውን ለዩ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላፈረሱ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ፊት ቅጣቸው። የእግዚአብሔርም ቍጣ ከእስራኤል ይርቃል።” ሙሴም የእስራኤልን ሕዝቦች፥ “እናንተ እያንዳንዳችሁ ብዔል ፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው። እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ወንድሙን ወደ ምድያማዊት ሴት ወሰደው፤ እነርሱም በምስክሩ ድንኳን ዳጃፍ ያለቅሱ ነበር። የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ። ያንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። ሁለቱንም እስራኤላዊውን ሰውና ምድያማዊቱን ሴት ሆዳቸውን ወጋቸው፤ ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተወገደ። በመቅሠፍቱም የሞቱት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። ስለዚህ አልሁ፦ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። ለአምላኩ ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና፥ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።” ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም የምድያም አባቶች ወገን የሚሆን የሳሞት ወገን አለቃ ነበረ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ምድያማውያንን አስጨንቋቸው፤ ግደሉአቸውም። ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና።”
ዘኍልቍ 25:1-18 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እስራኤላውያን በሰጢም በነበሩበት ጊዜ ወንዶቹ ከሞዓብ ሴቶች ጋራ ማመንዘር ጀመሩ። እነዚህም ሴቶች ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ሕዝቡን ጋበዙ፤ ሕዝቡም መሥዋዕቱን በላ፤ ለአማልክቱም ሰገደ። ስለዚህ እስራኤል በኣል ፌጎርን በማምለክ ተባበረ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በላዩ ነደደ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አስፈሪው የእግዚአብሔር ቍጣ ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ ግደልና በጠራራ ፀሓይ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ስቀላቸው” አለው። ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፣ “እያንዳንዳችሁ በኣል ፌጎርን በማምለክ የተባበሩትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው።” ከዚህ በኋላ ሙሴና መላው የእስራኤል ማኅበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ እያለቀሱ ሳለ፣ አንድ እስራኤላዊ እነርሱ እያዩት አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ ወደ ቤተ ሰቡ መጣ። የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ይህን ባየ ጊዜ ማኅበሩን ትቶ ጦሩን በእጁ በመያዝ፣ እስራኤላዊውን ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ፤ ጦሩንም ወርውሮ እስራኤላዊውንና ሴቲቱን አጣምሮ ወጋቸው። ከዚያም በእስራኤላውያን ላይ የወረደው መቅሠፍት ተከለከለ፤ ሆኖም በመቅሠፍቱ የሞተው ሰው ቍጥር ሃያ አራት ሺሕ ደርሶ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ እኔ ለክብሬ በመካከላቸው እንደምቀና ስለ ቀና ቍጣዬን ከእስራኤላውያን መልሶታል፤ ስለዚህ እኔም በቅናቴ ጨርሶ አላጠፋኋቸውም፤ ስለዚህ እነሆ እኔ የሰላም ቃል ኪዳኔን ከርሱ ጋራ እንደማደርግ ንገረው። ለአምላኩ ክብር ቀንቶ ለእስራኤላውያን ስላስተሰረየላቸው፣ እርሱና ልጆቹ ዘላቂ የክህነት ቃል ኪዳን ይኖራቸዋል።” ከምድያማዊቷ ሴት ጋራ የተገደለው እስራኤላዊ የሰሉ ልጅ ዘንበሪ ይባላል፤ የስምዖናውያን ቤተ ሰብ አለቃ ነበር። እንዲሁም የተገደለችዋ ምድያማዊት ሴት ከስቢ ትባላለች፤ እርሷም ከምድያማውያን ቤተ ሰብ የአንዱ ነገድ አለቃ የሆነው የሱር ልጅ ነበረች። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ምድያማውያንን እንደ ጠላት ቈጥራችሁ ፍጇቸው። ይኸውም ፌጎር ላይ በተፈጸመው ድርጊትና በፌጎር ምክንያት በመጣው መቅሠፍት በተገደለችው በምድያማዊው አለቃ ልጅ፣ በእኅታቸው በከስቢ አታልለው የጠላትነት ሥራ ስለ ሠሩባችሁ ነው።”
ዘኍልቍ 25:1-18 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር። ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ። እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው። ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፦ እናንተ ሁሉ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው። እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ምድያማዊቱን አንዲቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት፤ እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያለቅሱ ነበር። የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። በመቅሠፍትም የሞተው ሀያ አራት ሺህ ነበረ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል። ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና ምድያማውያንን አስጨንቁአቸው ግደሉአቸውም።
ዘኍልቍ 25:1-18 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
የእስራኤል ሕዝብ በሺጢም ሸለቆ ሰፍሮ በነበረበት ጊዜ ወንዶቹ እዚያ ከነበሩበት ሞአባውያን ሴቶች ጋር አመነዘሩ፤ እነዚያም ሴቶች ለሞአብ ጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት እንዲመገቡ ጋበዙአቸው፤ እስራኤላውያንም የመሥዋዕቱን ምግብ በልተው ፔዖር በሚባለው ተራራ ላይ ለሚገኘው በዓል ለተባለውም ጣዖት ሰገዱ፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን በፔዖር ለባዓል ጣዖት በመስገዳቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጣ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ላይ የነደደው ቊጣዬ ይበርድ ዘንድ የእስራኤልን መሪዎች ሁሉ ወስደህ በጠራራ ፀሐይ በሕዝብ ፊት ግደላቸው።” ሙሴም ለእስራኤል መሪዎች “እያንዳንዳችሁ ከየነገዳችሁ በዓል ለሚባለው የፒዖር ጣዖት የሰገደውን ሰው ሁሉ ግደሉ” ብሎ ትእዛዝ አስተላለፈ። ሙሴና መላው ማኅበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተገኝተው በሚያለቅሱበት ጊዜ ከእስራኤላውያን አንዱ አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ በእነርሱ ፊት በማለፍ ወደ ቤተሰቡ አቀረባት። የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ይህን ባየ ጊዜ ከተቀመጠበት በመነሣት ከጉባኤው መካከል ወጥቶ ሄደ፤ ጦርም አንሥቶ፥ ሰውየውና ሴቲቱ ወዳሉበት ድንኳን ገባ፤ ሁለቱንም በአንድነት በጦር ወግቶ ገደላቸው፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያንን በማጥፋት ላይ የነበረው መቅሠፍት ቆመ፤ ነገር ግን እስከዚያው ሰዓት ድረስ ያ መቅሠፍት ኻያ አራት ሺህ ሕዝብ አጥፍቶ ነበር። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባደረገው ነገር ምክንያት በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያለኝ ቊጣ በርዶአል፤ ፊንሐስ ከእኔ በቀር ለሌላ አምላክ የሚሰግዱትን መታገሥ አልፈለገም፤ በቊጣዬ እስራኤልን ያላጠፋሁትም እርሱ ስለ እኔ ባሳየው ቅናት ነው። ስለዚህ እኔ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር የሰላም ቃል ኪዳኔን የምሰጠው መሆኔን ንገረው። እርሱ ለእኔ ለአምላኩ ቀናተኛ በመሆኑና የሕዝቡንም ኃጢአት በማስተስረዩ እርሱና ዘሮቹ በሙሉ ለዘለዓለም ካህናት ይሆናሉ።” ከምድያማዊቱ ሴት ጋር የተገደለው እስራኤላዊ ስም የሳሉ ልጅ ዚምሪ ሲሆን እርሱም በስምዖን ነገድ ውስጥ የጐሣ አለቃ ነበር። የሴቲቱም ስም ኮዝቢ ይባል ነበር፤ “ጹር” ተብሎ የሚጠራው አባትዋም በአንድነት የሚኖሩ የጥቂት ምድያማውያን ጐሣዎች አለቃ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በምድያማውያን ላይ አደጋ ጥላችሁ ደምስሱአቸው፤ ይህንንም የምታደርጉት እናንተን በፔዖር በማታለል ግፍ ስለ ሠሩባችሁና በፔዖር በወረደው መቅሠፍት ምክንያት በተገደለችው በአለቃቸው ልጅ በኮዝቢ አማካይነት በፈጸሙት ሽንገላ ነው።”
ዘኍልቍ 25:1-18 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
እስራኤልም በሰጢም ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝር ጀመር። ሕዝቡንም ወደ አማልክቶቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ለአማልክቶቻም ሰገዱ። እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የጌታ የቁጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ላይ በጌታ ፊት ስቀላቸው።” ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፦ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው። እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ እያለቀሱ ሳሉ በእነርሱ ፊት ምድያማዊት የሆነችን አንዲት ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት። የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱንም ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። በመቅሠፍትም የሞተው ሰው ሀያ አራት ሺህ ነበረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቁጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። ስለዚህ እንዲህ በል፦ ‘እነሆ፥ የሰላም ቃል ኪዳኔን እሰጠዋለሁ። ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።’ ” ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ይባል ነበረ፤ እርሱም የስምዖናውያን ወገን የአባቱ ቤት አለቃ የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ትባል ነበረ፤ እርሷም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ምድያማውያን እንደ ጠላት ቁጠሩአቸው እነርሱንም ድል ንሱአቸው፤ በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሽንገላቸው ሸንግለዋችኋልና እነርሱን እንደ ጠላቶቻችሁ ቁጠሩአቸው።”