ዘኍልቍ 19:1-22
ዘኍልቍ 19:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጠዋለህ፤ ከሰፈር ወደ ውጭ ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዷታል፤ በፊቱም ያርዷታል። አልዓዛርም ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፤ ከደምዋም ወደ ምስክሩ ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። ጊደሪቱንም በፊቱ ያቃጥሏታል፤ ቍርበቷንም፥ ሥጋዋንም፥ ደምዋንም፥ ፈርስዋንም ያቃጥሉት። ካህኑም የዝግባ ዕንጨት ሂሶጵም፥ ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። ካህኑም ልብሱን ያጥባል፤ ገላውንም በውሃ ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውሃ ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል፤ ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰት ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ይነጹበታልና። የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ገላውንም ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል። “የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። እንደዚሁ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያነጻል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያነጻ ንጹሕ አይሆንም። የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያነጻ የእግዚአብሔርን ድንኳን ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። “ሰው በቤት ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ቤት የሚገባ ሁሉ በቤቱም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። በሜዳም የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን፥ ወይም የሰውን አጥንት፥ ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። ለአንጽሖ እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፤ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቅሉበታል። ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በቤቱም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን፥ ወይም የሞተውን፥ ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል። ንጹሑም በሦስተኛው ቀንና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ይነጻል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። “ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያነጻ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከማኅበሩ መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ነው። ይህ የዘለዓለም ሥርዐት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።”
ዘኍልቍ 19:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው፣ ሕጉ የሚጠይቀው ሥርዐት ይህ ነው፤ እንከን ወይም ነውር የሌለባትንና ቀንበር ተጭኖባት የማያውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጠው፤ ከሰፈሩ አውጥተውም በፊቱ ይረዷት። ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አቅጣጫ ሰባት ጊዜ ይርጨው። እርሱ እየተመለከተም ጊደሯን ያቃጥሏት፤ ቈዳዋም፣ ሥጋዋም፣ ደሟም፣ ፈርሷም ጭምር ይቃጠል። ካህኑ የዝግባ ዕንጨት፣ ሂሶጵና ብሩህ ቀይ ክር ወስዶ ጊደሯ በምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምር። ከዚህ በኋላ ካህኑ ልብሱን በውሃ ማጠብ፣ ሰውነቱንም መታጠብ አለበት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ሊመለስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። የሚያቃጥለውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ፣ ሰውነቱንም በውሃ መታጠብ አለበት፤ እርሱም ደግሞ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። “ንጹሕ የሆነ ሰው የጊደሯን ዐመድ ዐፍሦ ከሰፈሩ ውጭ በመውሰድ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ያኑረው፤ ይህም ርኩሰትን ለሚያነጻ ውሃ እንዲውል በእስራኤል ማኅበረ ሰብ የሚጠበቅ ይሆናል፤ ከኀጢአትም ለመንጻት ይጠቅማል። የጊደሯን ዐመድ የሚያፈስሰውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ አለበት፤ ያም ሰው እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤላውያን እንዲሁም በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች የሚሆን ዘላለማዊ ሥርዐት ነው። “የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛውም ቀን ሁለመናውን በውሃው ያንጻ፤ ንጹሕም ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ካላነጻ ግን ንጹሕ አይሆንም። የሞተን ሰው በድን ነክቶ ራሱን ያላነጻ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያም ሰው ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የሚያነጻው ውሃ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው፤ ከርኩሰቱም አልተላቀቀም። “አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ እንዲሁም ተከድኖ ያልታሰረ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል። “ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል። “ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት። ከዚያም በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ሰው ሂሶጵ ወስዶ በውሃው ውስጥ ከነከረው በኋላ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፣ እዚያ የነበሩትንም ሰዎች ሁሉ ይርጫቸው። እንዲሁም የሰው ዐፅም ወይም መቃብር ወይም ደግሞ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ሰው የነካው ማንኛውንም ሰው ይርጭ። የነጻው ሰው ያልነጻውን ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ይርጨው፤ በሰባተኛው ቀን ያንጻው፤ የሚነጻውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ ማምሻውም ላይ የነጻ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ የረከሰ ሰው ራሱን ሳያነጻ ከቀረ የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሷልና ከማኅበረ ሰቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ የሚያነጻው ውሃ ያልተረጨበት ስለ ሆነ ርኩስ ነው። ይህም ለእነርሱ የዘላለም ሥርዐት ነው። “የሚያነጻውን ውሃ የሚረጨውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ የሚያነጻውንም ውሃ የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል። የረከሰ ሰው የሚነካው ማንኛውም ነገር ይረክሳል፤ ይህን የነካ ሰው ደግሞ እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።”
ዘኍልቍ 19:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል። ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል። የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም። የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል። ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤ ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል። ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባይጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
ዘኍልቍ 19:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ይህ እኔ ያዘዝኩት የሕጉ ሥርዓት ነው፦ ነውር የሌለባትና በጫንቃዋ ላይ ቀንበር ተጭኖባት የማታውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡ ለእስራኤላውያን ንገሩአቸው። ጊደርዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ስጡት፤ ከሰፈርም ወጥታ በእርሱ ፊት ትታረድ፤ ካህኑ አልዓዛርም ከደሙ ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እያጠቀሰ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ እንስሳዪቱ በሙሉ ማለትም ቆዳዋ፥ ሥጋዋ፥ ደምዋና የሆድ ዕቃዋ ሁሉ በካህኑ ፊት ይቃጠል፤ ካህኑ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጵ ቅርንጫፍና ቀይ ክር ወስዶ ጊደርዋ በምትቃጠልበት በእሳት ውስጥ ይጣለው፤ ከዚህ በኋላ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብና ወደ ሰፈሩ ይመለስ፤ ነገር ግን ያልነጻ ሆኖ እስከ ማታ ድረስ ይቈይ፤ ጊደርዋን ያቃጠለውም ሰው ልብሱን አጥቦ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ እርሱም እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል። ከዚህ በኋላ ንጹሕ የሆነ ሌላ ሰው የጊደርዋን ዐመድ ሰብስቦ በመውሰድ ከሰፈሩ ውጪ ንጹሕ በሆነ ቦታ ያስቀምጠዋል፤ እዚያም ለእስራኤላውያን ጉባኤ ርኲሰትን ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ ለማዘጋጀት የሚጠቅም ይሆናል፤ ይህም ሥርዓት የሚፈጸመው ኃጢአትን ለማስወገድ ነው። ዐመዱን የሰበሰበው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ነገር ግን እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ ይህ የሥርዓት መመሪያ ለእስራኤላውያንና በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ የጸና ሕግ ሆኖ ይኖራል። “የማንኛውንም ሰው አስከሬን የሚነካ ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ለማንጻት በተመደበው ውሃ ራሱን ያነጻል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሱን የማያነጻ ከሆነ ሊነጻ አይችልም። ለማንጻት የተመደበው ውሃ በእርሱ ላይ ስላልፈሰሰ በድን ነክቶ ራሱን የማያነጻ፥ እንደ ረከሰ ይቈያል፤ እንዲህ ያለው ሰው ድንኳኑን ያረክሳል፤ ስለዚህም ከእስራኤል ሕዝብ ይለይ። “አንድ ሰው በድንኳኑ ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ ይህ ነው። እርሱ በሞተበት ጊዜ በዚያ ድንኳን ውስጥ ያለ ሰው ወይም ወደዚያ የሚገባ ሰው ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል። በድንኳኑ ውስጥ የሚገኝ ክዳን የሌለው ማንኛውም እንስራም ሆነ ማሰሮ የረከሰ ይሆናል። ሰው የገደለውን ወይም በሕመም የሞተውን ሰው በውጭ ወድቆ ሳለ ሬሳውን የሚነካ ሰው፥ ወይም የሰው ዐፅም፥ ወይም መቃብር የሚነካ ሰው ለሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል። “ርኲሰቱንም ለማስወገድ፥ ለኃጢአት ማስተስረያ ከተቃጠለችው ጊደር ዐመድ ጥቂት ተወስዶ በማሰሮ ውስጥ ይከተት፤ ንጹሕ የምንጭ ውሃም ይጨመርበት፤ ቀጥሎም ንጹሕ የሆነ ሰው የሂሶጵ ቅርንጫፍ ወስዶ በውሃው ውስጥ እየነከረ በድንኳኑና በውስጡ በሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ ላይ እንዲሁም በድንኳኑ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ይርጨው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ የሆነ ሰው ዐፅም ወይም ሬሳ ወይም መቃብር በነካው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን የነጻው ሰው ባልነጻው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤ በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ያነጻዋል፤ ያም ሰው ልብሱንና ገላውን ካጠበ በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ የነጻ ይሆናል። “ያልነጻና ራሱንም ያላነጻ ሰው ለማንጻት የተመደበው ውሃ በላዩ ስላልፈሰሰ የረከሰ ሆኖ ይቈያል፤ እንደዚህ ያለው ሰው የእግዚአብሔርን ድንኳን ስለሚያረክስ ከማኅበሩ ይለይ። ይህን ሕግ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ መጠበቅ ይኖርባችኋል፤ ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ በላዩ የሚረጨው ሰው ልብሱን ማጠብ ይኖርበታል፤ ውሃውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ ያልነጻ ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ የረከሰ ይሆናል፤ ያንንም ዕቃ የሚነካ ሌላ ሰው እስከ ማታ እንደ ረከሰ ይቈያል።”
ዘኍልቍ 19:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ጌታ ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። እርሷንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርሷም ከሰፈር ወደ ውጭ ትወሰዳለች፥ እርሷም በእርሱ ፊት ትታረዳለች። ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ይሰበስባል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኩሰትንም የሚያነጻ ውኃ ተደርጎ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። የጊደሪቱንም አመድ የሰበሰበው ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል። “የሞተውን የማናቸውንም ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን በውኃ ያነጻል፥ በዚህም ንጹሕ ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያነጻ ንጹሕ አይሆንም። የሞተውን ሰው በድን የነካ ማናቸውም ሰው ሁለመናውን ባያነጻ የጌታን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ ከርኩሰት የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኩሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። “ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። በተንጣለለው ሜዳ በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማናቸውም ሰው ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለረከሰው ሰው ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይጨመርበታል። ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ይነክረዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ ዐፅሙንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ ንጹሑም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ርኩስ በሆነው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያነጻዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በመሸም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል። “ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያነጻ፥ ያ ሰው የጌታን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። ይህም ለእነርሱ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ የሚረጨው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ከርኩሰትም የሚያነጻውን ውኃ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። የረከሰውም ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።”