ዘኍልቍ 14:20-24 - Compare All Versions
ዘኍልቍ 14:20-24 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣ ክብሬን ደግሞም በግብጽና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣ ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤ አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል።
ዘኍልቍ 14:20-24 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር እላቸዋለሁ፤ ነገር ግን ሕያው እንደ መሆኔና ክብሬም ምድርን የሞላ እንደ መሆኑ፥ ከእነዚህ ሕዝብ አንዱም ወደዚያች ምድር ለመግባት በሕይወት አይኖርም፤ በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ተአምራት ሁሉ አይተዋል፤ ነገር ግን የትዕግሥቴን ብዛት ደጋግመው በመፈታተን ለእኔ መታዘዝ እምቢ አሉ። ስለዚህ ለቀድሞ አባቶቻቸው ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር በፍጹም አይገቡም፤ እኔን ከናቁኝ ሰዎች መካከል አንድ እንኳ ወደዚያች ምድር ከቶ አይገባም። ነገር ግን አገልጋዬ ካሌብ ልዩ አመለካከት ስላለውና ለእኔ ያለውንም ታማኝነት ስላጸና ሄዶ የመረመራትን ምድር እሰጠዋለሁ፤ ዘሮቹም ያቺን ምድር ይወርሳሉ፤
ዘኍልቍ 14:20-24 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝ፤ ስሜም ሕያው ነው፤ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ ቃሌንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእኔ ጋር በዚህ ላሉ መልካምንና ክፉን ለይተው ለማያውቁ ልጆቻቸው፥ የሚያውቀው ለሌለ ለታናሹ ሁሉ ያችን ሀገር እሰጣታለሁ፤ ለጥፋት ያነሳሱኝ ሁሉ አያዩአትም። ወዳጄ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ በእርሱ ላይ ስለ ሆነና ስለ ተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።
ዘኍልቍ 14:20-24 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እግዚአብሔርም አለ፦ እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤ ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።
ዘኍልቍ 14:20-24 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ጌታም እንዲህ አለ፦ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የጌታ ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ክብሬንና ተአምራቴን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ እኔን ስለ ተፈታተኑኝ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፥ እነዚህም የናቁኝ ሰዎች ሁሉ አያይዋትም፤ ባርያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለ ተከተለኝ እርሱ ሄዶ ወደ ነበረበት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።