ዘኍልቍ 13:25-33 - Compare All Versions

ዘኍልቍ 13:25-33 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ምድ​ሪ​ቱ​ንም ሰል​ለው ከአ​ርባ ቀን በኋላ ከዚያ ተመ​ለሱ። ገሥ​ግ​ሠ​ውም በቃ​ዴስ ፋራን ምድረ በዳ ወዳ​ሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን፥ ወደ እስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ማኅ​በር ሁሉ ደረሱ፤ ወሬ​ው​ንም ለእ​ነ​ር​ሱና ለማ​ኅ​በሩ ሁሉ ነገ​ሩ​አ​ቸው፤ የም​ድ​ሪ​ቱ​ንም ፍሬ አሳ​ዩ​አ​ቸው። እን​ዲ​ህም ብለው ነገ​ሩት፥ “ወደ ላክ​ኸን ምድር ደረ​ስን፤ እር​ስ​ዋም ወተ​ትና ማር ታፈ​ስ​ሳ​ለች፤ ፍሬ​ዋም ይህ ነው። ነገር ግን በም​ድ​ሪቱ የሚ​ኖሩ ሰዎች ኀያ​ላን ናቸው፤ ከተ​ሞ​ቻ​ቸ​ውም የተ​መ​ሸጉ፥ እጅ​ግም የጸኑ ታላ​ላቅ ናቸው። ደግ​ሞም በዚያ የዔ​ና​ቅን ዘሮች አየን፤ በአ​ዜብ በኩል ዐማ​ሌቅ ተቀ​ም​ጦ​አል፤ በተ​ራ​ሮ​ች​ዋም ኬጤ​ዎ​ና​ዊ​ውና ኤዌ​ዎ​ና​ዊ​ውም፥ ኢያ​ቡ​ሴ​ዎ​ና​ዊው፥ አሞ​ሬ​ዎ​ና​ዊ​ውም ተቀ​ም​ጠ​ዋል፤ ከነ​ዓ​ና​ዊ​ውም በባ​ሕር ዳርና በዮ​ር​ዳ​ኖስ ወንዝ አጠ​ገብ ተቀ​ም​ጦ​አል።” ካሌ​ብም ሕዝ​ቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰ​ኘና፥ “አይ​ደ​ለም! ማሸ​ነ​ፍን እን​ች​ላ​ለ​ንና እን​ውጣ፤ እን​ው​ረ​ሳት” አለ። ከእ​ርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን ፥ “በኀ​ይል ከእኛ ይበ​ረ​ታ​ሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መው​ጣት አን​ች​ልም” አሉ። ስለ ሰለ​ሉ​አ​ትም ምድር ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች እያ​ወሩ፥ “እኛ ዞረን የሰ​ለ​ል​ናት ምድር የሚ​ኖ​ሩ​ባ​ትን ሰዎች የም​ት​በላ ምድር ናት፤ በእ​ር​ስ​ዋም ዘንድ ያየ​ና​ቸው ሰዎች ሁሉ ረጃ​ጅም ሰዎች ናቸው፤ በዚ​ያም ግዙ​ፋን የሆ​ኑ​ትን አየን፤ እኛም በእ​ነ​ርሱ ፊት እንደ አን​በ​ጣ​ዎች ሆን፤ እን​ዲ​ሁም በፊ​ታ​ቸው ነበ​ርን፤” እያሉ የሰ​ለ​ሉ​አ​ትን ምድር ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች አስ​ፈሪ አደ​ረ​ጓት።

ዘኍልቍ 13:25-33 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ምድሪቱንም ዐሥሠው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። ሰዎቹም፣ ሙሴና አሮን መላውም የእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ወዳሉበት በፋራን ምድረ በዳ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተመለሱ፤ ያዩትንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ አስረዱ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “ወደ ላክኸን ምድር ዘልቀን ገባን፤ ማርና ወተት የምታፈስስ ናት፤ ፍሬዋም ይኸው። በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ግን ኀያላን ሲሆኑ፣ ከተሞቹም የተመሸጉና ትላልቅ ናቸው፤ እንዲያውም የዔናቅን ዝርያዎች በዚያ አይተናል። አማሌቃውያን የሚኖሩት በኔጌብ፣ ኬጢያውያን ኢያቡሳውያንና አሞራውያን በኰረብታማው አገር፣ ከነዓናውያን የሚኖሩት ደግሞ በባሕሩ አቅራቢያና በዮርዳኖስ ዳርቻ ነው።” ከዚያም ካሌብ ሕዝቡን በሙሴ ፊት ጸጥ አሠኝቶ፣ “እንውጣ! ምድራቸውን እንውረስ፤ ማሸነፍም እንችላለን” አላቸው። ከእነርሱ ጋራ የወጡት ሰዎች ግን፣ “ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለ ሆኑ፣ ልናሸንፋቸው አንችልም” አሉ። እነዚህም ስለ ሰለሏት ምድር በእስራኤላውያን መካከል እንዲህ የሚል መጥፎ ወሬ አሠራጩ፤ “ያየናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ናት፤ እዚያ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ግዙፎች ናቸው፤ ኔፊሊምንም በዚያ አይተናል፤ የዔናቅ ዝርያዎች የመጡት ከኔፊሊም ነው። ራሳችንን ስናየው እንደ አንበጣ ነበርን፤ በእነርሱ ዐይን የታየነውም በዚሁ መልክ ነበር።”

ዘኍልቍ 13:25-33 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል። ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ። ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን፦ በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ። ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ፦ እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።

ዘኍልቍ 13:25-33 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ሰዎቹ ምድሪቱን ለአርባ ቀኖች ካጠኑ በኋላ ተመለሱ። በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወደነበሩት ወደ ሙሴና አሮን ወደ መላውም የእስራኤል ማኅበር መጡ፤ እነርሱም ያዩትን ነገር ሁሉ አስረዱ፤ ያመጡትንም ፍሬ አሳዩአቸው፤ ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፦ “ምድሪቱን አጥንተን በእርግጥም በማርና በወተት የበለጸገች አገር መሆንዋን ተረድተናል፤ ምድሪቱም የምታፈራው ፍሬ ዐይነት ይህ ነው፤ ነገር ግን በዚያች ምድር የሚኖሩ ሕዝብ እጅግ ብርቱዎች ናቸው፤ ከተሞቻቸውም ታላላቆችና የተመሸጉ ናቸው፤ ከዚህም ሁሉ በላይ እጅግ ግዙፋን የዐናቅ ዘሮች አይተናል። ዐማሌቃውያን በኔጌብ ምድር የሚኖሩ ሲሆን፥ ሒታውያን፥ ኢያቡሳውያንና አሞራውያን በተራራማው አገር፥ ከነዓናውያን ደግሞ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርና በሜዲቴራኒያን በባሕር ዳር ይኖራሉ።” ካሌብ ግን በሙሴ ፊት ሕዝቡን ጸጥ በማሰኘት “እነርሱን ድል ለመንሣት የሚያስችል በቂ ኀይል ስለ አለን አገሪቱን አሁኑኑ ሄደን እንያዛት አለ።” ከካሌብ ጋር ሄደው የነበሩት ሰዎች ግን “እኛ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ከቶ ኀይል የለንም፤ በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ከእኛ ይበልጥ ብርቱዎች ናቸው” ብለው ተናገሩ። ሊሰልሉ ስለ ሄዱበት አገርም ለእስራኤላውያን ያቀረቡት ዘገባ ተስፋ አስቈራጭ ነበር፥ እነርሱም፥ “ልንሰልል የሄድንበት አገር ወደ እርስዋ ለመኖር የሚመጣውን ሰው የምትውጥ ናት፤ እዚያ ያየናቸው ሰዎች ረጃጅሞች ናቸው። በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን የዐናቅን ዘሮች አይተናል፤ እኛ በእነርሱ ፊት ልክ እንደ ፌንጣ ያኽል ሆነን ነበር የታየነው፤ እነርሱም እንደዚያው አድርገው ሳይመለከቱን አይቀሩም” አሉ።

ዘኍልቍ 13:25-33 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። ተጉዘውም በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ መጡ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ወደ ላክኸን ምድር ገባን፥ እርሷም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው፤ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም ሰፋፊዎች ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።” ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ “ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ፥ እንውረሰው” አለ። ከእርሱ ጋር ወጥተው የነበሩት ሰዎች ግን፦ “ከእኛ ይልቅ እነርሱ ብርቱ ናቸውና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” አሉ። ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች አወሩ እንዲህም አሉ፦ “እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርሷም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን።”