ዘኍልቍ 13:17-26 - Compare All Versions
ዘኍልቍ 13:17-26 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፤ አላቸውም፥ “ከዚህ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ፥ ወደ ተራሮችም ውጡ። ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ቅጥር ያላቸው ወይም የሌላቸው እንደ ሆኑ፥ ምድሪቱም ለም ወይም ጠፍ፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች አይታችሁ፥ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤” ወራቱም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ነበረ። ወጡም፤ ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በኤማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። ወደ ምድረ በዳም ወጡ፤ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ዘሮች አኪማን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ ከተማ በፊት ሰባት ዓመታት ተሠርታ ነበር። ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆም መጡ፤ አዩኣትም፤ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፤ በመሎጊያም ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የወይን ዘለላ ሸለቆ ብለው ጠሩት። ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ከዚያ ተመለሱ። ገሥግሠውም በቃዴስ ፋራን ምድረ በዳ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
ዘኍልቍ 13:17-26 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ሙሴም ከነዓንን እንዲሰልሉ በላካቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ኔጌብን ዘልቃችሁ ወደ ተራራማው አገር ግቡ። ምድሪቱ ምን እንደምትመስልና የሚኖሩባትም ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፣ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች መሆናቸውን እዩ። የሚኖሩባት ምድር ምን ዐይነት ናት? መልካም ወይስ መጥፎ? የሚኖሩባቸውስ ከተሞች ምን ይመስላሉ? በግንብ ያልታጠሩ ናቸው ወይስ የተመሸጉ? ዐፈሩስ እንዴት ያለ ነው? ለም ወይስ ደረቅ? ደናም ወይስ ደን አልቦ? በተቻለ መጠን ከምድሪቱ በኵር ፍሬ ይዛችሁ ኑ።” ወቅቱ የወይን ፍሬ መብሰል የጀመረበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ ወጥተው ከጺን ምድረ በዳ አንሥቶ በሌቦ ሐማት በኩል እስከ ረአብ ድረስ ዘልቀው ምድሪቱን አጠኑ። በኔጌብ በኩል ዐልፈው አኪመን፣ ሴሲና ተላሚ የተባሉ የዔናቅ ዝርያዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን መጡ። ኬብሮን የተመሠረተችው ጣኔዎስ በግብጽ ምድር ከመቈርቈሯ ሰባት ዓመት አስቀድሞ ነበር። ወደ ኤሽኮል ሸለቆ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላ ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ይህንም ከሮማንና ከበለስ ጋራ በመሎጊያ አድርገው ለሁለት ተሸከሙት። እስራኤላውያን የወይን ዘለላ ስለ ቈረጡባትም ያች ስፍራ የኤሽኮል ሸለቆ ተባለች። ምድሪቱንም ዐሥሠው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። ሰዎቹም፣ ሙሴና አሮን መላውም የእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ወዳሉበት በፋራን ምድረ በዳ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተመለሱ፤ ያዩትንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ አስረዱ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
ዘኍልቍ 13:17-26 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም፦ ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤ ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥ ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ። ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። በደቡብም በኩል ወጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎእ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር። ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት። ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
ዘኍልቍ 13:17-26 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ሙሴም ሲልካቸው እንዲህ አላቸው፦ “በኔጌብ በኩል አድርጋችሁ ወደ ተራራማው አገር ውጡ። አገሪቱ ምን እንደምትመስል፥ ምን ያኽል ሕዝብ እንደሚኖርባትና የሕዝቡም ብርታት ምን ያኽል እንደ ሆነ መርምሩ፤ ምድሪቱ መልካም ወይም መጥፎ እንደ ሆነች፥ ሕዝቡም የሚኖሩት ግልጥ በሆኑ መንደሮች ወይም በተመሸጉ ከተሞች እንደ ሆነ አጥኑ። አፈሩ ለም፥ ምድሪቱም በደን የተሸፈነች መሆንዋን መርምሩ፤ አይዞአችሁ እዚያ ከሚገኘው ፍራፍሬ ይዛችሁ ኑ።” ወቅቱም የወይን ፍሬ መብሰል የጀመረበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ ሰዎቹ ወደ ሰሜን ሄዱ፤ በአገሪቱም ከሚገኘው ከጺን ምድረ በዳ ጀምረው ለሐማት መተላለፊያ ቅርብ እስከሆነው ረሖብ ድረስ አጠኑ። በመጀመሪያው ወደ ኔጌብ ሄደው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ይህችም ኬብሮን “ዐናቂም” ተብለው የሚጠሩ የግዙፋን ሰዎች ዘር የሆኑ አሒማን፥ ሼሻይ እና ታልማይ የሚባሉት ጐሣዎች መኖሪያ ነበረች። (ኬብሮን የተመሠረተችውም በግብጽ ምድር ጾዓን ተብላ የምትጠራው ከተማ ከመቈርቈርዋ ሰባት ዓመት ቀደም ብሎ ነበር።) አልፈውም ወደ ኤሾኮል ሸለቆ ደረሱ፤ ከዚያም የወይን ዘለላ ያለበትን ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ያንንም የወይን ዘለላ አንድ ሰው ብቻውን ሊሸከመው የማይችል ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ሁለት ሰዎች በመሎጊያ በትከሻቸው ላይ ተሸከሙት፤ ከዚህም ጋር የሮማንና የበለስ ፍሬ ይዘው መጡ። ያ ቦታ “የኤሽኮል ሸለቆ” ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት እስራኤላውያን የወይን ፍሬ ዘለላ ቈርጠው ያመጡበት ስፍራ ስለ ነበር ነው። ሰዎቹ ምድሪቱን ለአርባ ቀኖች ካጠኑ በኋላ ተመለሱ። በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወደነበሩት ወደ ሙሴና አሮን ወደ መላውም የእስራኤል ማኅበር መጡ፤ እነርሱም ያዩትን ነገር ሁሉ አስረዱ፤ ያመጡትንም ፍሬ አሳዩአቸው፤
ዘኍልቍ 13:17-26 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ሙሴም የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ላካቸው፥ እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “ከዚህ በኔጌብ በኩል አድርጋችሁ ውጡ፥ ወደ ተራራማውም አገር ሂዱ፤ ምድሪቱንም ምን እንደምትመስል፥ በእርሷም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ እዩ፤ እንዲሁም የሚኖሩባት ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም የተመሸጉ አምባዎች እንደ ሆኑ፥ ምድሪቱም ለም ወይም መካን፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች ተመልከቱ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ።” በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወቅት ነበረ። ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ ለሌብ ሐማት ቅርብ እስከሆነችው እስከ ረዓብ ድረስ ሰለሉ። በደቡብም በኩል ወጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብጽ ካለችው ከጣኔዎእ ከሰባት ዓመት በፊት የተቈረቈረች ከተማ ነበረች። ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ሙሉ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት። ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። ተጉዘውም በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ መጡ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።