ዘኍልቍ 11:24-30
ዘኍልቍ 11:24-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም ወጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመናው ወረደ፤ ተናገረውም፤ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተጨመረላቸውም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፤ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ዐረፈባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ፤ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፥ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። የሙሴ ምርጥ ባለሟል የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ ፥ ከልክላቸው” አለው። ሙሴም “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያሳድር አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
ዘኍልቍ 11:24-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው። ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም። ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋራ ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ። ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ቀንተህ ነውን? የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤ ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ።
ዘኍልቍ 11:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው። ሙሴም፦ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
ዘኍልቍ 11:24-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ሙሴ ወጥቶ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ መሪዎች ሰባውን በአንድነት ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ተናገረው፤ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ከፊሉን ወስዶ በሰባዎቹ መሪዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈስ በወረደባቸውም ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ፤ ይህን ያደረጉት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር። ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣት ወደ ሙሴ ሲሮጥ ሄዶ “ኤልዳድና ሜዳድ በሰፈር ውስጥ ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ሲል ነገረው። ከጐልማሳነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው!” አለው። ሙሴም “አንተ ስለ እኔ ትቈረቈራለህን? እኔስ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ መንፈሱን ቢያወርድና ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታዬ ነው!” አለው። ሙሴና ሰባዎቹ የእስራኤል መሪዎችም ወደ ሰፈር ተመለሱ።
ዘኍልቍ 11:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም ወጣ የጌታንም ቃላት ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። ጌታም በደመናው ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አኖረ፤ መንፈሱም በእነርሱ ላይ ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ ሲሆን የሁለተኛው ስም ደግሞ ሞዳድ ይባል ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን ወጥተው አልሄዱም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ ሆነው ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው” አለው። ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “የጌታ ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ ጌታም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያኖር፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።